አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ታሪክ ጠገብና የበርካታ ስልጣኔ ባለቤት ብትሆንም ፖለቲካችን በሃይለ ቃል ተጀምሮ በሃይል ርምጃ መደምደሙ ዋነኛ ስብራትችን ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ በኢትዮጵያ በሃይለ ቃል ተጀምሮ በሃይል ርምጃ የሚደመደም የፖለቲካ ባሕልን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ማቆም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ከኢፋት እስከ ጊቤ፣ ከወላይታ እስከ ከፋ፣ ከወሎ እስከ ሸዋ፣ ከላስታ እስከ ትግራይ፣ ከአፋር እስከ ሶማሌ የነበሩ የኢትዮጵያ ሱልጣኔቶች እና ሥርዎ መንግሥታት ሲፈተሹ በሁሉም ጊዜ የሚታየው ስብራት በሃይለ ቃል ጀምሮ በሃይል ርምጃ መደምደም መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህ የታሪካችን አሳዛኝ እና ዋነኛው ስብራት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ ይህን አስከፊ ታሪክ ለመጨረሻ ጊዜ መዝጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
“በውስጣችን ያሉ ችግሮች እኛው ጀምረን እኛው የምንጨርሳቸው ብቻ አይደሉም ፤የጠምባሮ አባቶች ከብት ሲገዛ የሌሉ አሞራዎች ከብት ሲታረድ በአካባቢው ያንዣብባሉ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሽ ሲል ያደፈጡና የሚነቁ የዘመናት ያልተቋረጠ የጠላትነት ስሜት ያላቸው ሀገራት አሉ” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በዚህ የሽብልቅ ጉዞ በእኛ ስንፍና የተጠቀሙ አሉ ፤ በቅርቡ እንኳን ቀይ ባሕርን ያጣንበት መንገድ የዚህ እኩይ ታሪካዊ ክስተት አንዱ መገለጫ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት ያስተዳደረችውንና በባለቤትነት የያዘችውን ቀይ ባሕር ያልተመረጠና ያልተወያየ መንግሥት በሸፍጥ ኢትዮጵያን የጂኦግራፊ እስረኛ እንድትሆን ያደረገበት ዋነኛው ምክንያት በውስጥ ያለ ስንፍና እንጂ በጠላቶች ሃይል አይደለም ነው ያሉት፡፡
ከዚህ በኋላ እነዚህ አሞራዎች እኩይ አላማቸውን ማሳካት እንዳይችሉ የውስጥ ችግሮችን በምክክር መፍታት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያን የውስጥ ልዩነት ለመጠቀም የሚፈልጉ አሞራዎች ኢትዮጵያ ከፍላጎቷ ውጪ የምትሰጠው አንድም ብሄራዊ ጥቅም እንደሌለ በማወቅ ቀልብ ግዙ ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ኢትጵያውያን ምንም እንኳን ቢጋጩ በሽምግልና፣ በይቅርታ እና በካሳ ወደ ቀደመ አንድነታቸው የሚመለሱ በመሆኑ አሞራዎች የሚያገኙት እድልና አጋጣሚ አይኖርም ነው ያሉት፡፡
በአቤል ነዋይ

