አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቀይ ባሕርን ያጣነው እኛ ስንጨቃጨቅ ጊዜ ጠብቀው ጣልቃ በመግባት መሻታችንን እንዳንከውን ባደረጉ ሃይሎች ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ በውይይት መፍታት የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ጉልህ ሚና አለው፡፡
ስለሆነም በምክክር ጉባዔው እኛ እና ከእኛ በፊት የነበሩ ሰዎች ያጧቸውን ጉዳዮች ዳግም ልጆቻችን እንዳያጡ በታላቅ ኃላፊነት መስራት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመው÷ ይህንን ችግር ወደ ዕድል መቀየር ከተቻለ የተሻለ ትውልድ መፍጠር ይቻላል፤ የምክክር ጉባዔውም ሀገርን የሚታደግና የሚገነባ ታሪክ ለመጻፍ ታላቅ ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተገኘውን እድል ሁሉ በመጠቀም በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የወታደራዊ ሪፎርም በማካሄድ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ ሆና የጂኦግራፊ እስረኛ የሆነችበት ዋና ምክንያት ያልተመረጠ እና ያልተወያየ መንግሥት በፖለቲካ ሸፍጥና ሴራ እንዲሁም የውስጥ መከፋፈልና ስንፍና መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ቀይ ባሕርን ያጣነው እኛ ስንጨቃጨቅ ጊዜ ጠብቀው ጣልቃ በመግባት መሻታችንን እንዳንከውን ባደረጉ ሃይሎች ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ይህ ታሪካዊ ክስተት እንደ አንድ እኩይ እሳቤ መገለጫ የሚጠቀስ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ የኢትዮጵያን መሻትና ጥቅም ማስቆም የሚችል ኃይል የለም፤ ያልተሳካልን በውስጥ ስንፍናችን እንጂ አቅም አጥተን አይደለም ብለዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ

