Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሀገር ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ደህንነት በዜጎች ጤና መጠበቅ ላይ የተመሰረተ ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9 ቀን 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዜጎችን ጤና መጠበቅ የሀገር ልማት፣ የኢኮኖሚ እድገት እና የብሔራዊ ደህንነት ዋነኛ መሰረት ነው አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፡፡

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ነው፡፡

በመርሐ ግብሩ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ እና ሌሎች አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ታዬ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ላለፈው አንድ ክፍለ ዘመን የሀገሪቱን የጤና ዋስትና ለማረጋገጥ ያደረገው ግስጋሴ የሚደነቅ ነው፡፡

ኢንስቲትዩቱ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ አያሌ ፈታኝ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የጤና ቀውሶችን፣ ወረርሽኞችን እንዲሁም የተላላፊ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ ግንባር ቀደም ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።

በተለይም እንደ ኮቪድ-19፣ የዝንጀሮ ፈንጣጣ እና ማርበርግ ያሉ በሽታዎችን ለመከላከል ያሳየው ፈጣን ምላሽና ሳይንሳዊ አመራር የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ጠንካራ ተቋማት የሀገር ግንባታ ምሰሶዎች በመሆናቸው መንግሥት ለተቋማት ግንባታና ጥንካሬ የሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ የተሰጡትን ሀገራዊ ተልዕኮዎች በብቃት መተግበር እንዲችል በመሠረተ ልማት እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ይበልጥ እንዲጎለብት እንደሚደረግ ገልጸው÷ ለዚህም አስቻይ የፖሊሲ መደላደልን በመፍጠር ረገድ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡

ተቋሙ እስካሁን ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ይበልጥ ለማላቅና ተግዳሮቶችን ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር መላው አመራርና ሰራተኛ የሳይንሳዊ ምርምር ብቃቱን ማሳደግ እንዳለበት አሳስበዋል።

በተለይም በቀጣዩ ምዕተ ዓመት ውጤታማና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የመከላከል ዝግጁነትና ምላሽ የመስጠት አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት

Exit mobile version