አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ዘርፉን ምርታማነት ይበልጥ ለማሳደግ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመተግበሩ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል አለ የግብርና ሚኒስቴር፡፡
በሚኒስቴሩ የግብርና ኤክስቴንሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚ የኔነሽ ኤጉ እንዳሉት÷ በግብራና ዘርፍ የተመዘገበውን አመርቂ ውጤት ለማስቀጠል ከተለመደው የአስተራረስ ዘዴ መውጣት ይገባል፡፡
ለዚህም ዘመኑን የዋጁ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በስፋት መጠቀምና የግብዓት አቅርቦትን ይበልጥ ማሳለጥ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የግብርና ቴክኖሎጂ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲሁም ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ ዘመናዊ ግብርናን እውን ለማድረግ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
የግብርና ሜካናይዜሽን ይበልጥ በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
ለአብነትም ከሳሳካዋ አፍሪካ አሶሴሽን፣ ከምርምር ተቋማት፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓትን ለማጠናከር ትኩረት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
ሳሳካዋ በገበያ ተኮር የእርሻ ልማት፣ በዲጂታል ኤክስቴንሽን አገልግሎትና በአግሪቢዝነስ ልማት ዘርፎች ላይ በመስራት ለአርሶ አደሮች ኑሮ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል፡፡
የሳሳካዋ አፍሪካ አሶሴሽን ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ፈንታሁን መንግስቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ተቋሙ በኢትዮጵያ ባለፉት 33 ዓመታት ለግብርና ዘርፍ እድገት በርካታ ሥራዎችን በማከናወን የራሱን አሻራ ማሳረፉን አስታውሰዋል፡፡
በፈጠራ የተደገፉ የኤክስቴንሽን አገልግሎቶችን እና ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋትና በትብብር የተመሰረቱ የአጋርነት ሥራዎችን ማሳደግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በቀጣይ የተገኙ ውጤታማ ተሞክሮዎችን በማስፋት የዲጂታል ግብርና፣ የግብርና ሜካናይዜሽን፣ የምርምርና ኤክስቴንሽን ሥራዎችን ማጠናከር ላይ ትኩረት ይደረጋል ማለታቸውንም ግብርና ሚኒስቴር ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
ለኢትዮጵያ ግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓት መዘመን ከፍተኛ ሚና ያበረከተው የሳሳካዋ አፍሪካ ዓመታዊ የባለድርሻ አካላት መድረክ “ከውጤት ወደ ተግባር” በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል፡፡

