አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለቀጣናው አዲስ የኃይል ልማት እና የትብብር ምዕራፍ ከፍቷል፡፡
ነገር ግን የግብፅ ሚዲያዎች እና የመንግሥት አካላት ጉዳዩን እንደ ውኃ እጥረት በማስመሰል ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።
የግድቡ መገንባት ሱዳንም ሆነ ግብፅ የሚያገኙትን የውኃ መጠን ፈጽሞ አልቀነሰም።
ኢትዮጵያ ለናይል ወንዝ ስርዓት ከ85 በመቶ እስከ 86 በመቶ የሚሆነውን አጠቃላይ የውኃ መጠን ታበረክታለች።
ይህ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የውኃ አስተዋፅኦ የሚመነጨው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ደጋማ ቦታዎች ሲሆን፣ በተለይም ዓባይ (ብሉ ናይል) ከጠቅላላው የናይል ፍሰት ከ59 በመቶ በላይ ድርሻ ይይዛል።
የቀረውን የውኃ መጠን የነጭ ናይል የሚያበረክቱ ሲሆን፣ ለናይል ወንዝ ውኃ መከበር ዋነኛ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ ለዘመናት የውኃ ድርሻዋን በአግባቡ የመጠቀም መብቷን ስትጠይቅ ቆይታ በሕዳሴው ግድብ አሳክታለች።
የሕዳሴ ግድብ ዋነኛ ዓላማም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንጂ የውኃ ፍሰቱን መቀነስ አይደለም።
የመደመር መንግሥት በተደጋጋሚ እንዳረጋገጠው፣ ግድቡ የውኃ ፍጆታን የማይጨምር በመሆኑ ለታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ማለትም ለሱዳን እና ለግብፅ የሚደርሰውን የውኃ መጠን ከቀድሞው ጋር ሲነጻጸር ምንም አይነት ቅነሳ አላሳየም።
እንዲያውም ግድቡ በሱዳን በኩል ለዓመታት ሲከሰት የነበረውን ጎርፍ ለመቆጣጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።
ይሁን እንጂ የግብፅ የዜና አውታሮች እና ባለስልጣናት ሰሞኑን ጉዳዩን ፕሮፓጋንዳ አድርገውታል።
በቅርቡ እንኳን የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ የናይል የውኃ ደህንነት ጉዳይ የማይደራደሩበት መሆኑን ገልጸዋል።
የዚህ ሁሉ የግብፅ የውዝግብ ፍላጎት መነሻ የዓባይን ውኃ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለመጠቀም ሳይሆን የቀጣናዊ የበላይነትን ለመቆጣጠር የሚደረግ ሩጫ መሆኑን በግልፅ ያሳያል።
ጉዳዩን በአግባቡ ካየን የግብፅ ባለስልጣናትና የሚዲያዎች ትኩረት በግድቡ የውኃ መጠን ላይ ሳይሆን፣ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶችን መሠረት አድርጎ በወንዙ ላይ የነበራቸውን ሙሉ የአንድ ወገን የተጠቃሚነት የበላይነትን ማስጠበቅ ነው።
የግብፅ አካሄድ ታሪካዊ ኢፍትሃዊነትን ለማስቀጠል እና አዲስ ቀጣናዊ ፖለቲካዊ የበላይነትን ለመያዝ የማለም ጉዳይ ነው፡፡
ግብፅ አሁንም በፈረንጆቹ በ1929 እና 1959 የተፈረሙትን ኢትዮጵያን ያላካተቱና አግላይ የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን ሙጥኝ በማለት አብዛኛውን የውኃ ድርሻ ለብቻዋ ለመቆጣጠር ትፈልጋለች።
ይህ አሰራር የተፋሰሱን የሌሎች ሀገራት ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት የሚጻረር ነው።
ግብፅ የዓባይን ጉዳይ የብሔራዊ ደኅንነቷ ማዕከል በማድረግ፣ በምስራቅ አፍሪካ እና በቀይ ባህር አካባቢ ካሉ ሌሎች ፖለቲካዊ ውዝግቦች ጋር በማስተሳሰር በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ትጠቀማለች።
በአጠቃላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ አፍሪካ የራሷን ሀብት ተጠቅማ እጣ ፈንታዋን የመወሰን አቅም እንዳላት ማሳያ ነው።
ግብፅ በግድቡ ምክንያት ውኃ ይጎድለኛል ብላ የምታስተጋባው ፕሮፓጋንዳ ሳይንሳዊ መሰረት የሌለው፣ ይልቁንም ያለፉትን ኢፍትሃዊ የውኃ ክፍፍል ስምምነቶች ለማስቀጠል እና በቀጣናው የበላይነትን ለመያዝ የምታደርገው ፖለቲካዊ ትርኢት ብቻ ነው።

