አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በየዘመኑ በታሪካዊ ጠላቶች እና በውስጥ ባንዳዎች ብትፈተንም ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት የእነኝህን ኃይሎች ፍላጎት እያከሸፈው ይገኛል አሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ።
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ሆለታ በሚገኘው የአካዳሚው ግቢ ያሰለጠናቸውን 71ኛ ዙር መተማ ኮርስ ዕጩ መኮንኖችን አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሰርዓቱ ላይ የተገኙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንዳሉት፤ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የምትገኘው ኢትዮጵያ በታሪካዊ ጠላቶች በየዘመኑ ስትፈተን ቆይታለች።
በታሪካዊ ጣላቶች እና በባንዳዎች የተሰራው የክፋት ደባ ጉዳት አላደረሰም ባይባልም ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ይህን እኩይ የጥፋት ሴራ በጀግንነት እያከሸፈ ይገኛል ብለዋል።
ኢትዮጵያም ፈተና ቢበዛባትም፤ ፈተናውን በጀግኖች ልጆቿ እያለፈች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ተመራቂዎችም ይህን አኩሪ ተጋድሎ ለማስቀጠል ለእናት ሃገራቸው በየዘመኑ መስዋዕትነት እየከፈሉ እንደሆነ ገልጸዋል።
አካዳሚው ኢትዮጵያን ያስቀጠሉ ጀግኖች መኮንኖችን ያፈራ የወታደራዊ የልህቀት ማዕከል እንደሆነም አብራርተው፤ አካዳሚው የስርዓተ ትምህርቱን ዘመኑ በሚጠይቀው እውቀት በማዘመን፣ በማሻሻል ለተቋማዊ ፕሮፌሽናሊዝም ምቹ መደላደል መፍጠሩን ጠቁመዋል።
ዕጩ መኮንኖች በስልጠና ያገኙት እውቀት የሚዳብረው በሚቀላቀሉበት የጦር ክፍል በተግባር በሚያገኙት ልምድ እና እውቀት በመሆኑ የቀሰሙትን እውቀት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው ማሳሰባቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል።

