Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከ23 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በ2018 በጀት ዓመት ከ23 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)።
ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በክልሉ በ2018 በጀት ዓመት በግብርና ዘርፍ የላቀ አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በእርሻ ዘርፍ በሁሉም የምርት ወቅቶች ከ801 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑንና የምርት ዕድገቱም ከ2014 መነሻ ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ60 ነጥብ 3 በመቶ ማደጉን አስረድተዋል።
በተጨማሪም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ5 ሺህ 700 ሄክታር በላይ ማሳ በማልማት ከ192 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን አመልክተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር 390 ሚሊየን ሊትር የወተት፣ 362 ሚሊየን እንቁላል፣ 79 ሺህ ቶን በላይ የማርና 81 ሺህ ቶን በላይ የስጋ ምርት ለገበያ ማቅረብ መቻሉንም አመልክተዋል።
ከ61 ሺህ ቶን በላይ ቡና ወደ ማዕከላዊ ገበያ በመላክ ከመነሻ ዓመቱ የ74 በመቶ እድገት መመዝገቡንና በሕገ ወጥ ቡና ዝውውር ቁጥጥርም 33 ሚሊየን ብር ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።
የኅብረት ሥራ ማህበራት ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 89 ሚሊየን ዶላር ያስገኙ ሲሆን፤ በአደጋ ስጋት ሥራ አመራርም 86 በመቶ የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ማሸጋገር ተችሏል ነው ያሉት።
በሰብል ምርምር 19 የገብስ ዘረ መሎች የተሰበሰቡ ሲሆን በአጃ፣ ሩዝ እና በተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎች ምርታማነት ላይ የሙከራ ጥናቶች መካሄዱን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል የገንዲ በሽታ ስጋት ጠቋሚ ካርታ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በማህበረሰብ አቀፍ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮጀክት 1 ሺህ 22 የዘር በጎች ተመርጠው 831 የተሻሻሉ በጎች ለአርሶ አደሩ መሰራጨታቸውን አንስተዋል።
በመጥፋት ላይ ያሉ ሀገር በቀል ዛፎችንና የሸኮ ዳልጋ ከብት ዝርያን የመጠበቅ ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት።
ከ88 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት የደን ሽፋኑን ከ43 ነጥብ 85 በመቶ ወደ 44 ነጥብ 65 በመቶ ማሳደግ የተቻለ ሲሆን፤ ከደን ውጤቶችም ከ11 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ የሮያሊቲ ክፍያ መሰብሰቡን አመልክተዋል።
የከተሞችን የቆሻሻ ችግር ለመቅረፍ በርካታ ስራ መሰራቱን ጠቅሰው ለ509 አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢና ማህበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ይሁንታ ፈቃድ መሰጠቱን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል።
Exit mobile version