Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አማራና ኦሮሞ በዘመናት መካከል ጠንካራ ውህደት መፍጠር የቻሉ ህዝቦች ናቸው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አማራና ኦሮሞ በዘመናት መካከል ጠንካራ ውህደት መፍጠር የቻሉ ህዝቦች ናቸው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሚኮ ጋር በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ባደረጉት ቆይታ፤ የአማራ እና የኦሮሞ ህዝቦችን ታሪካዊ ትስስር አስመልቶ አንስተዋል።

በዚህም ሁለቱ ህዝቦች በጋራ ሲዘምቱ፣ ሲነግዱ፣ ሲጋቡና በብዙ ሲዋሃዱ መኖራቸውን አብራርተዋል።

የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች በጋብቻ፣ በፖለቲካዊ ጋብቻ እና በባህላዊ ጉዲፈቻ ጠንካራ መስተጋብር መፍጠር መቻላቸውን ጠቅሰው፣ በእነዚህ ምዕራፎች በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለው ትስስር ይበልጥ መጠናከሩን አብራርተዋል፡፡

የተለያዩ የታሪክ ክስተቶች የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች ጠንካራ የታሪክ ውህደት እንዲኖራቸው ማድረጋቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በሸዋ፣ በጎንደር፣ በየጁ እና ሌሎች በርካታ ስልጣኔዎች ሁለቱ ህዝቦች የነበራቸውን ትስስር በማሳያነት አንስተዋል።

በዘመናዊት ኢትዮጵያ ምስረታ ሁለቱ ህዝቦች በጋራ መቆማቸውን አውስተው፣ በተለያዩ ዘመቻዎችም ድል ማድረጋቸውን ነው ያብራሩት፡፡

የዓድዋ ድል በውህደት የተሰራ፣ በጋራ የተፋለሙበት፣ ለአንዲት ውድ የከበረች ሀገር በጋራ ዋጋ የከፈሉበት፣ ሀገር አስቀድመው በጋራ ዘምተው በጋራ የሞቱበት፣ ሀገር ያፀኑበት የጋራ ድል እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

የዓድዋ ድል አፄ ምኒሊክ ከደጅአዝማች ባልቻና ከፊታውራሪ ገበየሁ ጋር በማበር እና በመተባበር ያሳኩት የጋራ ዓላማ እና ድል መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በፊውዳል ስርአቱ ላይ የጎጃምና የባሌ ገበሬዎች መብታቸውን ለማስከበር መንቀሳቀሳቸውን ጠቁመው፤ ይህ አብሮ የመኖርና የመዋሃድ ባህልና ሁኔታም በሁለቱ ብሔሮች ብቻ ሳይሆን በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚስተዋል ነው ብለዋል፡፡

Exit mobile version