አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እውነተኛ ጥያቄ ያላቸው ዳያስፖራዎች ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት በቅርበት ሊሰሩና ሊሳተፉ ይገባል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር በወቅታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸው ካነሷቸው ቁልፍ ጉዳዮች መካከልም በዳያስፖራው ማሕበረሰብ አካባቢ የሚስተዋለው የጎራ መለዋወጥ አንዱ ነው፡፡
በዚህም አንዳንድ የዳያስፖራ አባላት በለውጡ ሒደት ጎራ መለወጣቸውን አንስተው÷ ለዚህም ሶስት ጉዳዮችን እንደምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡
አንዳንድ የዳያስፖራ አባላት በለውጡ ላይ የነበራቸው የተሳሳተ ስሌት አንዱ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ አካላት ራሳቸውን የለውጡ ጀማሪ፣ መሪ፣ አዋላጅ እና ባለቤት አድርገው ወስደዋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ስለሆነም እኔ በፈለኩት መንገድ ካልመራሁት ወደሚል የተሳሳተ ስሌት መግባታቸውን ጠቁመው÷ “ከቻልኩ መንገስ፣ ካልቻልኩ ማንገስ አለብኝ የሚል ዕምነት ያላቸው ግለሰቦች ነበሩ” ብለዋል፡፡
እነዚህ ግለሰቦች ለውጡ በብዙ ሰዎች ጥረት፣ ተሳትፎ፣ መስዋዕትነት የመጣ እና በተሳታፊዎቹ የሚመራ እንጂ የግለሰቦች ፍላጎትን ለማሳካት የመጣ አለመሆኑን ሲረዱ የጎራ ለውጥ አድርገዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በአንዳንድ የዳያስፖራ አባላት ዘንድ ለጎራ መቀያየር በምክንያትነት ያነሱት ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ ከዩቲዩብ ንግድና ጥገኝነት ለመጠየቅ ሲባል መቃወም፣ ማንቋሸሽና መቃረን ብቸኛ መንገድ አድርገው የወሰዱ ሰዎች ናቸው ብለዋል፡፡
አንዳንድ የዳያስፖራ አባላት አቋም ለመቀያየር በሶስተኛ ደረጃ ምክንያት አድርገው የጠቀሱት እውነተኛ ጥያቄ ኖሯቸው በበቂ ሁኔታ አልተመለሰልንም ብለው የሚያምኑ ሰዎች ጎራ ሊቀይሩ ይችላሉ ነው ያሉት፡፡
ስለሆነም እውነተኛ ጥያቄ ያላቸው ቀርበው በመመልከት እና በመጠየቅ አብረውን ሊሰሩ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)”÷ ለውጥ ዳር በመቆም አይሳካም፤ ተሳትፎ ያስፈልጋል” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “ለውጥ የአንድ ሰሞን ድግስ አይደለም፤ ሒደት ነው፡፡ በዛ ሒደት ውስጥ ብዙ ጉዳዮች ሊቀያየሩ ይችላሉ፤ ረጅም መንገድ መሆኑን አምኖ፣ ራስን አስተምሮ ማስተካከል ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡
ለርካሽ ዓላማና ጥቅም ሲባል ቁም ነገር ማጉደል አይሁንባቸው፣ ከታሪክ ቀኝ ቁሙ ሲሉም መክረዋል፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ
ለውጥ ዳር በመቆም አይሳካም፤ ተሳትፎ ያስፈልጋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

