አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የወልቃይት ጥያቄን ለአጭር ጊዜ ደስታ ብለን ብንመልሰው ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ አደጋ ይሆናል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር በወቅታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል ለረጅም ጊዜ አከራካሪ ሆኖ የቆየውን የወልቃይት ወሰንና ማንነት ጥያቄ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በጉዳዩ ላይ ሁለቱም ክልሎች የየራሳቸው ጥያቄና ቅሬታ እንዳላቸው አንስተዋል።
በትግራይ ክልል በኩል ቦታው በህገ መንግስታዊ ስሪቱ በትግራይ ስር የነበረና በጦርነት ምክንያት ያጣነው በመሆኑ ሊመለስልን ይገባል የሚል ጥያቄ እንዳለ ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል በኩል ደግሞ ቦታው በህግ አግባብና በተሟላ መንገድ ወደ አማራ ክልል መመለስ ሲገባው የፌዴራል መንግሥት አልመለሰም የሚል ወቀሳ እንደሚሰነዘር አብራርተዋል።
ይሁን እንጂ የፌዴራል መንግሥት እጁን ቢያወጣ በኃይልም ቢሆን እናስመልሳለን የሚሉ አካላት እንዳሉ ጠቅሰው፤ አንዱን ወገን ብቻ አስደስቶ ሌላኛውን ወገን በጥያቄ ውስጥ የሚተው ውሳኔ ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ እንደማይችል አጽንኦት ሰጥተዋል።
ለአጭር ጊዜ እፎይታና ደስታ ተብሎ የሚሰጥ ምላሽ መልሶ ግጭት የሚፈጥርና ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ አደጋ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የመደመር መንግሥት መርህ ሚዛናዊነትና ሙሉ እይታ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ ቀደም የነበረው የፌዴራል ስሪት በህዝቦች ሰፊ ውይይት ባለመደረጉ ምክንያት ጥያቄው ለረጅም ጊዜ ሊቀጥል መቻሉን አመልክተዋል፡፡
በመሆኑም ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በትዕግስት፣ በውይይት፣ በህግና ስርዓት የሁለቱንም ክልል ህዝቦች ኢትዮጵያውያን በመሆናቸው አሳምኖ በሚሄድ መንገድ መፈታት እንዳለበት አሳስበዋል።
የወልቃይትና መሰል የወሰን ጥያቄዎች በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ባለው ሀገራዊ ምክክር ውስጥ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸው ዘላቂ መፍትሔ ያገኛሉ ተብሎ ተስፋ እንደሚደረግና ጉዳዩን በአጭር ጊዜ ስሜት ከመጋለብ ይልቅ በትዕግስትና በሰላማዊ መንገድ ማየት ብቸኛው አማራጭ መሆኑን አመልክተዋል።
በሶስና አለማየሁ

