Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል በሚቀጥሉት 25 ዓመታት ከተሜነት በተሟላ ደረጃ ይስፋፋል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአማራ ክልል በሚቀጥሉት 25 ዓመታት ከተሜነት በተሟላ ደረጃ ይስፋፋል አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገራዊ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በአማራ ክልል በገጠር ያለው ነዋሪ የመብራት፣ የውሃ፣ የጤና የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኝ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም በክልሉ በሚቀጥሉት 25 ዓመታት ከተሜነት በተሟላ ደረጃ ይስፋፋል ብለዋል፡፡

በመስኖ፣ በቴክኖሎጂ፣ ምርታማነትን የማሳደግ ጉዳይ አሁን ካለው ጋር ለውድድር የሚበቃ ነው ብዬ አላስብም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አምራች ዘርፉ፣ ኢንዱስትሪው በብዙ ደረጃ ይቀየራል ሲሉ ጠቁመዋል።

የዲጂታል ኢኮኖሚ በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት እንደሚረጋገጥ አንስተዋል።

አሁን ያለው ትውልድ በከፋፋይ፣ በውሸት፣ መሰረት በሌለው ታሪክ ላይ ቆሞ የሚነታረክ መሆኑ አብቅቶ የሚጠቅመውንና የሚፈይደውን የሀገርን ጥቅም ማዕከል ያደረገውን ትርክት ገንብቶ ለጋራ ጥቅም መረባረብ እንዳለበትም አመልክተዋል።

አማራን ብቻ ሳይሆን አካባቢን የሚጠቅም ብልጽግና እናረጋግጣለን፤ ብልጽግናውንም የሚያስተዳድር ትውልድን አብረን እንፈጥራለን ብለዋል።

ይህ ጉዳይ የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ ገልጸው፤ ይህ ትውልድ ስራውን ከሰራ መጪው ትውልድ የተሻለ ህይወት እንደሚኖረውና የአማራም ህዝብ ከዚህ እንደሚጠቀም ተስፋ አደርጋለሁ ነው ያሉት፡፡

Exit mobile version