አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል ታሪካዊ መርሐ ግብር በይፋ መጀመሩን አብስረዋል።
በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል ታሪካዊ መርሐ ግብር ዛሬ መጀመሩን አስመልክቶ ሚኒስትሯ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ አረንጓዴ ዐሻራችንን ይዘን ወደ መሬት የምንወርድበት ትልቅ ምክንያት የደረቀች የነጠፈች የተጎዳች ምድር ስላለችን ነው፡፡
ዛሬ 800 ሚሊየን አረንጓዴ ችግኞች ወደ መሬት ዝቅ ብለው መሬትን ይዳስሳሉ፤ መሬትም ቃሏን የምታጸናበትንና የተቀበለችውን መልሳ በእጥፍ መስጠት እንደምትችል የምታሳይበት ልዩ ቀን ነው ብለዋል።
በዘንድሮው ክረምት 8 ቢሊየን ችግኞችን እንተክላለን ብለን እቅድ ይዘናል ብለው የምንተክለው በሃሳብ እና በተግባር አንድነት ሲሉ ተናግረዋል።
በተግባርና በሃሳብ የምንሄድበት ትልቁ መንነሻ ደግሞ የመደመር መንግሥት ኑ በአንድነት የተጎሳቆለች እና የነጠፈችውን ምድራችንን እናክማት በሚል ሃሳብ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
800 ሚሊየን ችግኞች፣ በተግባር እና በሐሳብ አንድነት በመደመር ዕሳቤ እናሳካለንም ነው ያሉት፡፡
በሶስና አለማየሁ

