አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በስምንት ዓመታት ቀጣይነት ባለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል፡፡
አረንጓዴ ዐሻራ በሕዝባዊ ቁርጠኝነትና ኢትዮጵያውያን በጋራ በመሆን አረንጓዴና ዘላቂነት ያለው ነገን መገንባት ይችላሉ በሚለው የጋራ እሳቤ እየተመራ ይበልጥ እየጠነከረ መቀጠሉን ተናግረዋል፡
ዛሬ ኢትዮጵያውያን ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ ዘላቂ ዐሻራ ለማሳረፍ በጋራ የሚሰባሰቡበት ዓመታዊው የአንድ ጀምበር ሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብራችን ነው ሲሉ አውስተዋል።
ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር እንዲሁም ከኮፕ32 ብሔራዊ ኮሚቴ ጋር በመሆን የራሳችንን ዐሻራ በማሳረፍ ለዚህ የጋራ ጉዞ የበኩላችንን አስተዋፅኦ አበርክተናል ነው ያሉት።
የተቀመጠውን 800 ሚሊየን ችግኝ የመትከል ታላቅ ግብ ለማሳካት በጋራ እየሰራን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ኢትዮጵያውያን ቀኑን ሙሉ ጥረታቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

