አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በመጀመሪያዎቹ 8 ሰዓታት ውስጥ ከ21 ሚሊየን በላይ ዜጎች 650 ሚሊየን ገደማ ችግኞችን ተክለዋል አሉ።
መርሐ ግብሩ የሕዝቡ ከፍተኛ ተሳትፎና የተግባር ቁርጠኝነት የታየበት መሆኑን ገልጸው፥ በቀሪው ሰዓታት 800 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል ዕቅዳችንን ለማሳካት ይሰራል ነው ያሉት፡፡
አረንጓዴ ዐሻራ ከችግኝ ተከላ ባሻገር ተስፋን፣ አንድነትን፣ የሀገር ፍቅርን እና ለቀጣይ ትውልድ ዘላቂ ሀብት የመተው ዕሴትን የሚያጠናክር ሀገራዊ ንቅናቄ መሆኑን አስረድተዋል።
በመርሐ ግብሩ የአካባቢ ሥነ ምህዳርን ለመጠበቅ ሀገር በቀል የዛፍ ዝርያዎችን መትከል፣ የአፈር መሸርሸርን መከላከልና አረንጓዴ ሽፋንን ማስፋፋት ቀዳሚ ትኩረት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የፍራፍሬ ችግኞችን በስፋት መትከል የምግብ ዋስትናን፣ የገቢ ፈጠራንና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንዳለው አንስተዋል፡፡
በአቮካዶ ምርት የተመዘገበው የወጪ ንግድ መሻሻል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር ለኢኮኖሚ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም በዚህ ዘርፍ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ ሰፊ ዕድል መኖሩን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የሀገሪቱ የልማት ጉዞ ዘላቂ መሠረት የሚያገኘው የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅና አረንጓዴ ልማትን በማስፋፋት መሆኑንም አመልክተዋል።
በዛሬው ዕለት በተለያዩ አካባቢዎች እስከ 100 ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ እንዳላቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሥራው አድካሚ ሊሆን ቢችልም በተገባው ቃል መሠረት ተስፋን ለመትከል ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ጥቁመዋል።
ይህም የአፈርና የአካባቢ ጥበቃንና የኢኮኖሚ ልማትን በአንድነት የሚያስቀጥል መሆኑን ጠቁመው፥ የተያዘው ዕቅድ እስከሚሳካ ድረስ ዜጎች በጽናት እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዮናስ ጌትነት

