Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አዲሱ የቁልፍ መሠረተ ልማቶች ደህንነት አዋጅ የሳይበር ምህዳሩን ለማጠናከር ወሳኝ ማዕቀፍ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲሱ የቁልፍ መሠረተ ልማቶች ደህንነት አዋጅ የሳይበር ምህዳሩን ለማጠናከር ወሳኝ ማዕቀፍ ነው አሉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ።

ዋና ዳይሬክተሯ የአዋጁን መፅደቅ አስመልክተው በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም አዋጁ የኢትዮጵያን የሳይበር ምህዳር በአስተማማኝ መሠረት ለመገንባትና የዲጂታል እምነትን ለማስፈን የተነደፈ ታሪካዊ የሕግ ማዕቀፍ ነው መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተለይም 12 የቁልፍ መሠረተ ልማት ዘርፎችን በመለየት ከሳይበር ደህንነትና ከተለያዩ የደህንነት ስጋቶች የሚጠበቁበትን የሕግና የቁጥጥር ሥርዓት ዘርግቷል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በፍጥነት ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ እየተሸጋገረች በመሆኑ የዲጂታል ሥርዓቶችን፣ መረጃዎችንና ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን ከሳይበር ስጋት መጠበቅ የብሔራዊ ደህንነትና የዲጂታል ሉዓላዊነት ጉዳይ እንደሆነም አመልክተዋል።

አዋጁ በቁልፍ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደርሱ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል፣ ስጋቶችን በቅድሚያ ለመለየትና ክስተቶች በሚያጋጥሙበት ወቅት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የተደራጀ የሕግና የአሠራር ሥርዓት የሚዘረጋ መሆኑን ጠቁመዋል።

እነዚህ ተቋማት በተገቢው የሳይበር ደህንነት ደረጃ እንዲጠበቁ አዋጁ ግዴታዎችን ማስቀመጡን ዋና ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።

ተቋማት የሳይበር ስጋት ምዘና እንዲያካሂዱ፣ የደህንነት ኦዲት እንዲያደርጉና አስፈላጊውን የደህንነት ሥርዓት እንዲዘረጉ የሚያስገድዱ አሠራሮች ተካትተዋል ነው ያሉት፡፡

በዚህ የዝግጅት ወቅት ተቋማት የአዋጁን መስፈርቶች እንዲያሟሉ አስተዳደሩ የቴክኒክ ድጋፍና መመሪያ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የቁልፍ መሠረተ ልማቶች ጥበቃ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ሰኔ 2 /2018 ዓ.ም መፅደቁ ይታወሳል።

በግዛቸው ግርማዬ

Exit mobile version