Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሸኔ ከሚጠላቸውና ሲያስሩት ከነበሩ ቡድኖች ጋር ትብብር እየፈጠረ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሸኔ የተነሳበትን አላማ በመርሳት በአማራ ክልል እና ትግራይ ክልል ካሉ ሸኔዎች ጋር ትብብር እየፈጠረ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦቢኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ በኦሮሚያ ክልል በአሁኑ ወቅት ስላለው የሰላም ችግር ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በኦሮሚያ ክልልና በሀገሪቱ እየታዩ ያሉ ችግሮች የተለያዩ መነሻ ምክንያቶች እንዳሏቸው አስረድተዋል፡፡

አንደኛው ችግር ወደ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ የፖለቲካ ሽግግር መሰል ባህሪ አለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ታፈኖ በሃይል ሲተዳደር የነበረውን ፖለቲካ ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ክፍት ሲደረግ መሰል አይነት ባህሪ ያሳያል ብለዋል፡፡

በሒደቱ ሁሉም ተመጣጠኝ ሃይል አለኝ ብሎ ስለሚያምንና በሃይል ፍላጎቱን ለማሳካት፤ በሃይል ስልጣን ለመያዝ ፤በሃይል የፈለገውን ማድረግ እንደሚችል በማመን ትንሽ መተሻሸት እንዲሁም መረባበሽ በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ታሪክ የሚታወቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ሥርዓት ስለ ዴሞክራሲ ለመለማመድ ዝግጁ እንዳልነበር ይታወቃል፤ አፍኖ በሃይል እየገዛ ነበር ነው ያሉት፡፡

ሃይል ቀርቶና ሚዲያ ተስፋፍቶ ሁሉም ሰው የፈለገውን ተናግሮ መኖር ሲጀምር አንዳንድ የሚደረጉ ልምምዶች እንደሚኖሩ ጠቁመው÷ እንደዚህ አይነት ፖለቲካ በሌሎች ሀገራትም እንደሚከሰት አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ መጀመሪያ መሰል ባህሪ ቢኖም በኋላ ላይ ተረጋግቶ ወደ ውይይት መሻጋገሩ አይቀርም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፡፡

ከተለያዩ መነሻዎች በመነሳት በሃይል የፈለኩትን መፈጸም እችላለሁ የሚል ሃይል ሁሉ አሁን አንድ በአንድ ብትመረምር መልስ ታገኛለህ ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ለምሳሌ ሸኔ ሲተቸን የነበረው ከብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር ትብብር በመፍጠር የኦሮሞን ጥያቄ ረስቶና ክዶ በራሱ ሥልጣን ይዟል የሚል ነው ብለዋል፡፡

ለዚህ መፍትሄው ደግሞ መንግሥትን ታግዬ በማሸነፍ ያልኩትን ድል ማምጣት እችላልሁ ብሎ ያምን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ብቻየን አልችልም ብሎ በማመኑ ከሚጠላቸውና ሲወቅሳቸው ከነበሩ ቡድኖች ጋር ትብብር ካልፈጠርኩ እያለ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ሳቢያም በአማራ ክልል እና ትግራይ ክልል ካሉ ሸኔዎች ጋር ትብብር እየፈጠረ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በአማራ ክልል ያሉ ሸኔዎች ደግም ትናንት ሸኔ በኦሮሚያ ውስጥ ችግር እየፈጠረ ነው፤ መንግሥት ዜጎችን ከሸኔ እየጠበቀ አይደለም ፤ በሸኔ ላይ ርምጃ መውሰድ አለበት በሚል ጥያቄ መታገል መጀመራቸውን አስታውሰዋል፡፡

አሁን ደግሞ ብቻችን ይህን መንግሥት ምንም ማድረግ አንችልምና ከሸኔ ጋር ትብብር ካልፈጠርን እያሉ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

በተመሳሳይ ወያኔ ትናንት ከእኔ ውጭ ውጊያ የሚችልና የሚያሸንፍ የለም፤ ከእኔ ውጪ ሀገር ማስተዳደር የሚችል የለም፤ ብቻየን ተዋግቼ ሁሉንም ጠራርጌ ስልጣን እመልሳለሁ ስትል ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ብቻየን አልችልም ክልል 3 ካለው ሸኔ ጋር እንጂ እያለች ነው ብለዋል፡፡

ይህም እነዚህ ሃይሎች በሒደት እየተዳከሙ በመምጣታቸውና የመንግሥት ሃይል ጠንካራ መሆኑን በማመን በጋራ እንጂ ብቻ ለብቻ አንችልም እያሉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህም አልቆሙም፤የውጭ ሃይሎችን ኤርትራና ሱዳንን ጋብዘውተጨማሪ ሃይል እየፈለጉ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህም ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ሽግግር በውስጥ አንድነት እየጠነከረ በመምጣቱ በጋራ በመሆን ተመጣጣኝ ሃይል ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡

ይህም አይሆንም እንደተለመደው ድል የእኛ ነው ፤ ምክንያቱም ጥያቄያችን ትክክል ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version