Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በዕውቀትና በተግባራዊ ክህሎት የተጠናከረ የሰው ኃይል መገንባት ወሳኝ ነው – ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ያላትን ሀብትና ጸጋ በአግባቡ ተጠቅማ የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል እንድትችል በዕውቀትና በተግባራዊ ክህሎት የተጠናከረ የሰው ኃይል መገንባት ወሳኝ ነው አሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል።
የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት በ2018 ዓ.ም ሥልጠናቸውን ያጠናቀቁ ከ1 ሺህ 898 በላይ ሰልጣኞችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ለኢትዮጵያ ዕድገትና ብልጽግና የሚያስፈልግ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን ማጠናከር አስፈላጊ ነው፡፡
በመደመር መንግሥት የሰው ኃይል ልማትን ከሀገራዊ የምርታማነትና የኢንዱስትሪ ሽግግር ጋር በማስተሳሰር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም የሙያ ብቃት ያላቸው ዜጎችን ማፍራት እንደ ዋነኛ የልማት መሠረት መወሰዱን አብራርተዋል።
በዚህ አቅጣጫም በኢንስቲትዩቱ 11 የለውጥ ትግበራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፤ ተመራቂዎቹ ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ለሀገራዊ ልማት እንዲያውሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በበኩላቸው ተቋሙ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ለሀገሪቱ የሰው ኃይል ልማት የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ትምህርትና ሥልጠና በተማረ የሰው ሀብት አቅርቦት ላይ ብቻ ሳይወሰን የቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግ፣ ምርምርና ፈጠራን ማበረታታት እንዲሁም ለኢንዱስትሪው የሚያስፈልገውን ብቁ ባለሙያ ማቅረብ ላይ ያተኮረ መሆኑንም አመልክተዋል።
በዕለቱ ከተመረቁት የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች መካከል የደቡብ ሱዳን ዜጎች እንደሚገኙበት ተጠቁሟል፡፡
በግዛቸው ግርማዬ
Exit mobile version