አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ ዙሪያ ያዘጋጀው የልምድ ልውውጥ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወጣቶች የ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭን እንዲቀላቀሉና የክረምቱ ወቅት ከመጠናቀቁ በፊት የተሳታፊዎችን ቁጥር ወደ 7 ሚሊየን ለማድረስ ሀገራዊ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ የተካሄደው የልምድ ልውውጥ መርሐ ግብር የዘርፉን መሪዎችና ፖሊሲ አውጭዎች፣ የምስክር ወረቀት ያላቸውን የኢኒሼቲቩን ተመራቂዎችና ወጣት ባለሙያዎችን በአንድነት ያገናኘ ነው።
ተሳታፊዎች ተሞክሯቸውንና እይታቸውን በመድረኩ እንዲያካፍሉ መደላድልን በመፍጠር መርሐ ግብሩ በተግባራዊ ዲጂታል ክህሎት ልማት አማካኝነት ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 አጀንዳ ዕድገት የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩም በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የወጣቶች የቴክኒክና የዲጂታል ክህሎት ብቃት ወሳኝ ሀገራዊ ሀብት ነው፡፡
በዚህ ክረምት የኮደሮችን ቁጥር 7 ሚሊየን ለማድረስ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበውን ጥሪ ተግባራዊነት አረጋግጠዋል።
መርሐ ግብሩ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ባተኮረ የኤግዚቢሽን ጉብኝት የተጀመረ ሲሆን፥ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ በኢኒሼቲቩ ዙሪያ ልምዳቸውንና እይታቸውን ያካፈሉ አራት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ አብዮት ባዩ (ዶ/ር)፣ የጊሮ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቤተልሔም ደሴ እንዲሁም የኢኒሼቲቩ ምሩቃን የሆኑት አዝመራው ታደሰ እና የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪዋ ማህሌት ሥዩም በፓናሉ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች ናቸው።
ተሳታፊዎችና ወጣቶች ክህሎታቸውን ያለማቋረጥ እንዲያሳድጉ፣ በተግባር ላይ ያተኮሩ መፍትሔዎችን እንዲያበለጽጉና በኢትዮጵያ የዲጂታል ሥነ ምህዳር ዕድገትና ፈጠራ ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ የውይይቱ ተሳታፊዎች አበረታትተዋል።
ወጣት ተሳታፊዎች የዲጂታል ክህሎትን የተመለከቱ ጥያቄዎችን ለፓናሊስቶች አቅርበው ምላሽ ያገኙበት ሲሆን ፥ አጠቃላይ መርሐ ግብሩ ግልጽ ውይይትና የልምድ ልውውጥ የተስተናገደበት መሆኑን ጽ/ቤቱ ገልጿል።
ይህ የልምድ ልውውጥ የ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ የዲጂታል ክህሎትን ለማሳደግና ሀገራዊ ለውጥን ለማፋጠን ያለውን ከፍተኛ ሚና በድጋሚ ያረጋገጠ ሆኗል።

