አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ወጣት መልካም ዓላማን አንግቦ የሚንቀሳቀስ፣ የለውጥ ዋነኛ ሞተርና የሉዓላዊነታችን ጽኑ ማገር ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ ኢትዮጵያን ከወጣቶቿ ነጥሎ ማየት እንደማይቻል አስገንዝበዋል፡፡
የሕዝባችን የእድሜ ስብጥር እንደሚያመላክተው ወጣቶች ከፍተኛውን ቁጥር መያዛቸው፣ ብልጽግናን ለማረጋገጥና ለማፅናት ታላቅ እድል ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣት መልካም ዓላማን አንግቦ የሚንቀሳቀስ፣ የለውጥ ዋነኛ ሞተርና የሉዓላዊነታችን ጽኑ ማገር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የኢትዮጵያ ወጣት የሀገሩን ታሪክ በአዲስ ብዕርና ብራና እየጻፈ ይገኛል ብለዋል።
ሀገራችንን የኋሊት ጠፍንገው የያዟትን አጓጉል ልማዶች፣ አላስፈላጊ ንትርኮች፣ ጭቅጭቅ እና ግጭቶች በመራቅ የአሁን ወጣት በልማት ላይ አተኩሯል፤ ድህነትን ተጠይፏል ነው ያሉት።
የመደመር መንግሥት የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና የአመራርነት ሚና ለማጠናከር በትኩረትና በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሀገራዊ ራዕይን ዕውን ለማድረግ ሁሉም ዜጋ በንቃት እየተጋ በፍቅር እንዲመላለስም ጥሪ አቅርበዋል።

