አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ንቦች በዓለማችን ላይ ካሉ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ጥቃቅን ፍጥረታት መካከል ይመደባሉ።
የእፅዋትን የአበባ ብናኝ በማዘዋወር ረገድ የሚጫወቱት ሚና ለምግብ ዋስትና እና ለብዝሃ ሕይወት ህልውና ወሳኝ መሰረት ነው።
ዛሬ የዓለም ዓቀፍ የማር ንብ ቀን ነው፡፡ ቀኑ እነዚህን ድንቅ ሰራተኞች የምናስብበት ቀን ብቻ ሳይሆን፣ ከሰው ልጅ ጋር ያላቸውን የተፈጥሮ ትስስር ከግምት አስገብተን ይበልጥ ለመሥራት የምንነሳሳበት ነው።
ኢትዮጵያ ንቦችን ጨምሮ ሌሎች ነፍሳት፣ እንስሳት እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብቶች በሙሉ ምህዳሩን በጠበቀ መንገድ ከሰው ልጆች ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ለማድረግ ዘላቂ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።
የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ወግ፣ ባህልና እሴት ከተፈጥሮ ጋር በሰላም የመኖር ጥልቅ ታሪክ አለው። በተለምዷዊ የእርሻ እና የንብ ማር ማነብ ልምዶቻችን ውስጥ፣ ዛፎችን አለመቁረጥ፣ የዱር እንስሳትንና ነፍሳትን መጠለያ እንዳያጡ በጥንቃቄ መንከባከብ የማህበረሰባችን መመሪያ ነበር።
ይህ ለተፈጥሮ ሃብት ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ባህላዊ እሴት፣ ዛሬም ድረስ በዘመናዊ የልማት ስራዎቻችን ውስጥ መሠረት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። የሰው ልጅ ህልውና ከተፈጥሮ ጥበቃ ጋር በቀጥታ የተሳሰረ መሆኑን ማህበረሰባችን ገና ከጥንት ጀምሮ የተረዳው እውነታ ነው።
ባለፉት ሰባት ዓመታት በሀገሪቱ እየተተገበረ የሚገኛው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ይህንን ታሪካዊና ባህላዊ የተፈጥሮ ጥበቃ ሂደት ይበልጥ እያጠናከረው ይገኛል። በዚህ ታላቅ ሀገራዊ መርሐ ግብር የሚተከሉ በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞች ዝም ብለው የሚተከሉ ሳይሆን፣ በጥንቃቄ የተመረጡና ለአካባቢው ስነምህዳር ተስማሚ የሆኑ ናቸው።
በተለይም ለንቦችና ለሌሎች የአበባ ብናኝ አዘዋዋሪዎች የሚሆኑ፣ የተለዩና አበባዎችን የሚሰጡ ዕፅዋት በስፋት እንዲተከሉ እየተደረገ ነው።
ይህ ተግባር ለንቦች ዘላቂ የምግብ ምንጭ በመሆን ምቹ የሆነ ስነ ምህዳር ከመፍጠሩም በላይ፣ ለሀገር በቀል የማር አናቢዎች አዲስ የተስፋ ብርሃን ፈጥሯል። ንቦች የአበባ ዱቄትና ማር የሚቀስሙባቸው ዛፎች መበራከታቸው የማር ምርትን በጥራትና በመጠን ለመጨመር አስችሏል።
በዚህም ምክንያት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአካባቢን አረንጓዴነት ከመመለስ ባለፈ፣ የንቦችን ህልውና በመጠበቅና የአናቢዎችን ኑሮ በማሻሻል ረገድ ሁለንተናዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በንብ ማነብና በማር ምርት ያላት አቅም በአፍሪካ ያላትን መሪነት የሚያረጋግጥ እና በዓለም አቀፍ ገበያም ላይ ተወዳዳሪነቷን እያሳደገ የመጣ ዘርፍ ነው።
በአህጉር አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ የንብ ማነብ ስራ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ሀገሪቱ በየዓመቱ የምታመርተው የማር መጠን በአፍሪካ አንደኛ ደረጃ ላይ የሚያስቀምጣት ሲሆን፣ ይህም ከአህጉሩ አጠቃላይ ምርት ከፍተኛውን ድርሻ ይሸፍናል።
በዓለም አቀፍ ደረጃም እንደ ቻይና፣ አርጀንቲና እና ቱርክ ካሉ ግዙፍ አምራቾች ቀጥሎ ስሟ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ሀገራት ተርታ ትሰለፋለች።
ይህንን ደረጃ እንድታገኝ ያደረጋት ዋነኛው ምክንያት የሚመረተው ማር ጥራትና ልዩ ተፈጥሯዊ ባህርይ ነው። ምርቱ ከቤት ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለኢንዱስትሪ፣ ለውበት መጠበቂያ እና ለህክምና ዘርፎች መዋል መቻሉ የዘርፉን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ያሳያል።
እኛ ዓለም አቀፍ የማር ንብ ቀንን ስናስብ፣ የነዚህን ትናንሽ ነፍሳት ታላቅ አስተዋፅዖ በመረዳት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር አማካኝነት እያከናወነች ያለችው የችግኝ ተከላ ስራ፣ የንቦችን ስነምህዳር በመጠበቅና በማበልጸግ ረገድ ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ተግባር ነው።
የተፈጥሮ ሚዛንን የጠበቀ አብሮነትን ማጠናከር የሰው ልጅ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲበለፅግ ያደርጋል።
ስለሆነም፣ ባህላዊ እሴቶቻችንን ከዘመናዊ አረንጓዴ ልማት ጋር በማጣመር የንቦችንና የተፈጥሮን ደህንነት የመጠበቅ ሀገራዊ ጥረታችን ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

