Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን የመረጃ ተቋማት በጋራ ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን የመረጃ  ተቋማት  በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል ከደቡብ ሱዳን የውጭ ኢንተለጀንስ ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ቶማስ ዱዝ ጋር በሁለቱ አገራት ፀጥታና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።

ከውይይቱ በኃላም የመረጃ ተቋማቱ ህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርንና ሽብርተኝነትን በጋራ በመከላከል እንዲሁም በድንበር አካባቢዎች የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ተባብረው ለመሥራት ተስማምተዋል።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፥ የአገልግሎቱ መስሪያ ቤት ዳይሬክተር ጀነራል ኮሚሽነር ደምላሽ ገብረ ሚካኤል ከደቡብ ሱዳን አቻቸው ከሜጀር ጀነራል ቶማስ  ዱዝ ጋር ባደረጉት ውይይት በደቡብ ሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎቹ በትብብር ማስቆም ለሁለቱም አገራት ሰላምና ደህንነት ፋይዳው ከፍተኛ በመሆኑ ችግሩን ከምንጩ ለመፍታት መረጃ በመለዋወጥ ረገድ በቅርበት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

እንዲሁም በውይይቱ የአገሮቻቸውን ብሄራዊ ጥቅም ሊጎዳ የሚችል እንቅስቃሴ የሚያደረግን አካል ሴራን በማክሸፍ ጭምር መረጃን መሰረት ያደረጉ ስራዎችን በመስራትና በመከላከል እንዲሁም አስቀድሞ በማወቅ ላይ ያተኮረ መሆኑን ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በመግለጫ አመልክቷል።

የሁለቱ  አገራት  የመረጃ ተቋማት ኃላፊዎች  በአካባቢው አገራት የጋራ  የደህንነት ስጋት እየሆነ በመጣው ህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ ሽብርተኝነት፣ ድንበር ዘለል ወንጀል፣ የአካባቢና  ቀጣናዊ የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ላይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን  ህዝቦች ከሚጋሯቸው ባህልና እሴቶች አኳያ በአቅም ግንባታ መስክም በጋራ ለመስራት ስምምነት ፈጽመዋል።

በዚህ ዙሪያ በተለይም ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ካለው የካበት ልምድ አንፃር ለደቡብ ሱዳን የመረጃ ተቋም የአቅም ግንባታ ሰልጠና እንደሚያመቻች በአገልግሎት መስሪያ  ቤቱ  ዳይሬክተር  ጀነራል በኩል ተገልፆል፡፡

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በቀጣናዊና አካባቢያዊ የፀጥታና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትብብር እንዲኖር የበኩላቸውን በጎ አስተዋጽኦ  ማድረግ እንደሚችሉ ሁለቱ ኃላፊዎች  በውይይታቸው ወቅት መግለፃቸውን ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

Exit mobile version