አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያና ቻይና ላኪዎች ከ340 ሚሊየን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው 33 የንግድ ለንግድ ግብይት ኮንትራት ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የኢትዮ ቻይና ወጪ ንግድ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
መድረኩ የኢትዮጵያና የቻይናን ዘላቂና ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ወደ ላቀ የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር ለማሸጋገር እንዲሁምየንግድ አማራጮች ለማስተዋወቅ ያለመ ነው፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ የስምምነቱ ዓላማ የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ገቢ ግኝት ለማሳደግ የሚያስችል የፕሮሞሽን ሥራዎችን በቻይና ለማካሄድ ያስችላል፡፡
33 የሚጠጉ ስምምነቶች መፈረማቸውን ገልጸው÷ እነኝህም 340 ሚሊየን ዶላር ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ስምምነቱን ወደ ትልቁ የቻይና ገበያ ለመግባት በቻይና መንግሥት የተቀረጸው ኢኒሼቲቭ አካል መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
በቡና፣ በቅባት እህል፣ በጥራጥሬ፣ በቆዳ፣ በማዕድን ምርቶች እና በጨርቃ ጨርቅ ላይ ከስምምነት መደረሱንናስምምነቱ ከቃል በዘለለ ተግባራዊ ውጤት የተገኘበት ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ምርቶች በዓለም ገበያ የሚያስተዋውቅና ተወዳዳሪነታቸውን በማሳደግ የተያዘውን ውጥን የሚያሳካ ነው ማለታቸውን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
የቻይና ንግድ ሚኒስቴር የውጭ ንግድ ዲፓርትመንት ም/ዋና ዳይሬክተር ቻንግ ሁይ በበኩላቸው ÷ የቻይና መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር አጠናክሮ ለመቀጠልና የገበያ ዕድል ይበልጥ ለማስፋፋት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የቻይና አስመጪዎች ጥራት ያላቸውን የኢትዮጵያ ምርቶች በስፋት ለመግዛትና ዘላቂ የንግድ ድልድይ ለመገንባት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

