Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ የሽግግር ጉዞ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ሀገር ዘላቂና ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚረጋገጠው ጤናማና አምራች ማኅበረሰብ መፍጠር ሲቻል ነው። የጤና አገልግሎትን በጥራትና በስፋት ተደራሽ ማድረግ ደግሞ ጤናማና አምራች ማኅበረሰብን ለመገንባት መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታ ነው።

በታዋቂው የታሪክ ተመራማሪ ዩቫል ኖአህ ሐራሪ “ሆሞ ዴውስ” በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደሚገልጹት፤ የሰው ልጅ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ካስመዘገባቸው ትልልቅ ድሎች አንዱ ወረርሽኞችን ከመከላከል አልፎ በራሱ ሳይንሳዊና ተቋማዊ አቅም መቆጣጠር መቻሉ ነው።

ኢትዮጵያም ባለፉት አምስት ዓመታት በጤናው ዘርፍ ያከናወነችው መጠነ-ሰፊ የማሻሻያና የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ ሀገሪቱ ከመሠረታዊ በሽታ መከላከል አልፋ፣ “አክሞ የማዳን” እና የወረርሽኝ አደጋዎችን በራስ አቅም በመመከት “የጤና ሉዓላዊነት” ደረጃ ላይ መድረሷን ያበሰረ ነው።

ይህ ስትራቴጂካዊ ሽግግር በዋናነት በሦስት ዐበይት አዕማድ ላይ የተመሠረተ ነው – የፋይናንስ አቅምን ማሳደግ፣ የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ማመረትን ማጎልበት እና ዲጂታላይዜሽን።

መንግሥት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ስለመስጠቱ ማሳያው በየዓመቱ የጤና በጀት እየጨመረ መምጣቱ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት ከነበረበት 70 ቢሊዮን ብር ወደ 130 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰኔ ወር 2017 ዓ.ም ከጤና ባለሙያዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት መግለጻቸው ይታወሳል።

ሀገሪቱ በሕክምና ግብዓቶች ራሷን እንድትችል በተደረገው ጥረት፣ የሕክምና ኦክስጅን የሚያመርቱ ተቋማት ድርሻ ከ3 በመቶ ወደ 58 በመቶ ማደጉን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

እንዲሁም የሀገር ውስጥ የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ አምራቾች ብዛት ከ8 በመቶ ወደ 41 በመቶ በማደጉ፣ የውጭ ጥገኝነትን ከመቀነሱም በላይ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን ማዳን ተችሏል።

የአፍሪካ የጤና መረጃ መሠረተ ልማት ካፕሱል ጥናት እንደሚያመላክተው፤ ኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ እስከ ገጠር ቀበሌዎች የሚደርሱ ከ17 ሺህ በላይ የጤና ኬላዎችንና ከ22 ሺህ በላይ የመንግሥት የሕክምና ተቋማትን ያቀፈ የጤና መዋቅር ገንብታለች። ከአፍሪካ በሕዝብ ቁጥር ሁለተኛ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ በዚህ መጠን ግዙፍ ሕዝብ ማገልገል የሚችል የጤና ሥርዓት መዘርጋቷ ትልቅ ተቋማዊ ስኬት ነው።

አዲስ አበባን የአፍሪካ የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በተቀመጠው ራዕይ መሠረትም፣ በከተማ አስተዳደሩ ሆስፒታሎች የነበረው የሕክምና አልጋዎች ቁጥር ከ1 ሺህ 384 ወደ 4 ሺህ 195 እንዲያድግ ተደርጓል።

በየዓመቱ እስከ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በጀት በመደጎም 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ነዋሪዎችን የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ መረጃ ያመላክታል።

ይህ እያደገ የመጣው የጤና ሥርዓት ሀገሪቱ ድንገተኛ አደጋዎችን እና በሽታዎችን የመመከት አቅሟን በተግባር አሳይቷል። ለዐብነትም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጂንካና አካባቢው በሕዳር ወር 2018 ዓ.ም. ተከስቶ የነበረውን የማርበርግ ቫይረስ የስርጭት መጠን ሀገሪቱ በራሷ የሕክምናና የቅኝት አቅም መቆጣጠር መቻሏ በዘርፉ ያካበተችውን አቅም ማሳያ ነው።

እነዚህ ተጨባጭ አፈጻጸሞች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት አጉልተውታል። ሀገሪቱ ከ40 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የጤና ሚኒስትሮች፣ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካዮችና ተመራማሪዎች የሚሳተፉበትን 76ኛውን የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ጉባኤ ማስተናገዷ፣ ለጀመረችው ሁለንተናዊ የጤና ዘርፍ ሪፎርም የተሰጠ ትልቅ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና ነው።

በታሪኩ ለገሰ

 

Exit mobile version