አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የንጹህ ታዳሽ ኃይል ልማት ፍሰት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ትስስር እና የውጭ ምንዛሪ ግኝት ቁልፍ ሚና እየተጫወተ መምጣቱ በተግባር እየታየ ነው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም እንደሚያሳየው፣ ተቋሙ በዓመቱ ያስመዘገበው ድምር ውጤት ሀገሪቱ በሃይድሮ ፓወር እና በሌሎች ታዳሽ ኃይል መስኮች ላይ የያዘችው ስትራቴጂካዊ ርዕይ ወደ ተጨባጭና የላቀ ውጤት እየተሸጋገረ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።
በበጀት ዓመቱ ከውጭ ሀገራት የኃይል ሽያጭ ብቻ 475 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ዛሬ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ(ኢ/ር) ተናግረዋል።
ይህ አኃዝ ከቀድሞው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ25 በመቶ ዕድገት ያሳየ ሲሆን ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የምታደርገው የኃይል አቅርቦት እያደገ መሄዱን እና የቀጣናው የኢነርጂ ማዕከል የመሆን አቅሟን በግልጽ ያሳያል።
በአጠቃላይ ከተመረተው የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ የውኃ ማመንጫዎች 97 በመቶ ድርሻ መያዛቸው ደግሞ ሀገሪቱ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋ ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ በሆነ መንገድ እየተጠቀመችበት መሆኑን ያመላክታል።
የማመንጨት አቅሙን 9 ሺህ 730 ሜጋ ዋት ማድረስ የቻለውና የ23 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አፈጻጸም፣ በተቋሙ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የ124 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ገቢ በመሰብሰብ የ39 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ እንዲመዘገብ አስችሏል።
የዕቅዱን 101 ነጥብ 83 በመቶ ማሳካት መቻሉ የስትራቴጂክ እቅድ አፈጻጸም ብቃትን ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ነፃነት እና የዲፕሎማሲ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ከፍ የሚያደርግ ነው።
ለቀጣይ ዓመታት የተያዙት የትኩረት አቅጣጫዎች ይህንን ስኬት ይበልጥ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ናቸው።
በቀጣይም የገናሌ ዳዋ 6 የውኃ ኃይል ማመንጫ፣ የአይሻ 2ኛ የንፋስ ኃይል ማመንጫና በሀገር ውስጥ ፋይናንስ የሚገነባ የ100 ሜጋ ዋት የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር እቅድ ተይዟል።
በተጨማሪም የአይሻ ንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ 40 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል ይጠበቃል።
እነዚህ ተነሳሽነቶች ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ያላትን የአረንጓዴ ልማት አርዓያነት ከፍ ከማድረግም አልፎ፣ የጂኦፖለቲካና የኢኮኖሚ አቅሟን በተማከለ መልኩ እያጠናከረች መሆኗን በግልጽ ያሳያሉ።

