አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ድሬዳዋ፤ የበረሃዋ ንግሥት ይሏታል! ትንሿ ኢትዮጵያ በሐረርጌ ደጋማ ምድር ግርጌ የምትገኝ፣ በሙቀትና በውበት የምትታወቀው የባቡር ሐዲድ ትንፋሽ የፈጠራት ድንቅ ከተማ ናት።
ዛሬ ድሬዳዋ የድሮ ትውስታዎቿንና የሰፈሮቿን ስነ ጽሑፋዊ ናፍቆት ሳትለቅ፣ የኢንዱስትሪ፣ የንግድ ማዕከልነቷን እንደያዘች ዘመናዊነቷን እንዳስጠበቀች ታላቅ የኮሪደር ልማት እያስተናገደች ትገኛለች።
ይህ የኮሪደር ልማት ተራ የመንገድ ግንባታ ሳይሆን፤ የከተማዋን ነፍስ ከዘመናዊ የከተማ ፍልስፍና ጋር የማዋሃድ ጥበብ ነው።
ይህች የኢንዱስትሪ መጀመሪያና የከተማ ማስተር ፕላን የተጀመረባት ለኪነ ጥበብ ቅርብ ሆና ሁሌም የምትናፈቅ፣ በድምጻውያን አንደበት የተዘፈኑላት ውብ ስንኞች የከተማዋን ሕያውነት ይመሰክራሉ።
ታዋቂው ድምጻዊ ጎሳዬ ተስፋዬ “ከጥንት አንስቶ እስከ ዛሬ ሲዘፈን ኖሯል ለድሬ ፤እኔም አለሁሽ እላለሁ መች አንደበቴን አስራለሁ ..” እያለ ስለ ከተማዋ ውበትና ናፍቆት ሲያንቆረቁር፣ የድሬዳዋ ልጅ የሆነው ድምጻዊ አሊ ቢራ በበኩሉ በአፋን ኦሮሞ ዜማዎቹ የከተማዋን የባህል ብዝሃነትና የወንድማማችነት ስሜት በክብር አንስቷል።
ዛሬ ያ የተዘፈነላት ውብ አየርና ፍቅር፣ በኮሪደሩ ልማት አማካኝነት ሌላ አዲስ መልክና ዘመናዊ መዋቅር ተላብሷል። የቀደሙት ስንኞች የናፍቆት ነበሩ፤ የዛሬዎቹ ግን የዕድገትና የውበት ምስክር ሆነዋል።
ታሪካዊቷ እና የንግድ ማዕከል የሆነችው ድሬዳዋ ታሪካዊ ቅርሶቿን ከዘመናዊ የከተማ መሠረተ ልማት ጋር በሚያስማማ ሁኔታ በተጀመረው የልማት ፕሮጀክት፣ ነዋሪዎችንና ጎብኚዎችን የሚስቡ ዘመናዊና ምቹ መዝናኛዎችን እየፈጠረች ይገኛል።
ይህ የከተማ ዘመናዊነት ራሱን የቻለ ጥልቅ ፍልስፍና አለው። ለዘመናዊ ከተማ ግንባታ ስኬት፣ ታዋቂዋ አሜሪካዊት የከተማ ጥናት ምሁርና ደራሲ ጄን ጃኮብስ “The Death and Life of Great American Cities” በተሰኘው ቀዳሚ መጽሐፏ ላይ ከተሞች ለሁሉም ሰው የሚሆኑት፤ በሁሉም ሰው በጋራ ሲገነቡና ሲታሰቡ ብቻ እንደሆነ በፅኑ ትሞግታለች።
ከተማ መገንባት ያለባት ለተሽከርካሪዎች ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች መሆኑን የምታነሳው ጃኮብስ፤ የድሬዳዋ ኮሪደር ልማት በትክክል የዚህን ፍልስፍና ፈለግ እንዲከተል አድርጋለች ማለት ይቻላል።
ሰፊ የሳይክልና የእግረኛ መንገዶች፣ የሕዝብ መዝናኛ አረንጓዴ ስፍራዎች እና ክፍት ቦታዎች በምድር በባቡርና ማርያም ቤተክርቲያን አካባቢ እንዲሁም በጥንታዊው የኮኔል ገበያ ስፍራ በተሰራው የኮሪደር ልማት ተፈጥረዋል፡፡ በዚህም ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ሕያው እና ተደራሽ እያደረጋት ነው።
ድሬዳዋ የሰፈሮቿ ስም ብቻ ሳይሆን የታሪክ ማህደርም በመሆኗ፤ እያንዳንዱ ሰፈር የራሱ የስነ-ጽሑፍ ጥልቀትና ትረካ አለው። በአሁኑ ወቅት የከተማዋን ሰፋፊ ክፍሎች በማካተት በተለያዩ ምዕራፎች በመተግበር ላይ ያለው የኮሪደር ልማት እነዚህን ታሪካዊ ሰፈሮች አዲስ ገጽታ እያላበሳቸው ይገኛል።
የውጪ ዜጎችና የባቡር ሰራተኞች መኖሪያ የነበረችውና የዘመናዊቷ ድሬዳዋ መነሻ የሆነችው ከዚራ፤ ዛሬ በኮሪደሩ ውበት ተኳኩላ ጥንታዊ የስነ ሕንጻ ይዘቷን ሳታጣ በዘመናዊ መብራቶችና ንጹሕ መንገዶች አሸበርቃለች።
የከተማዋ የልብ ትርታና የትራፊክ መገናኛ የሆነው መገንጠያ ደግሞ በአረንጓዴ ተክሎችና ውብ የትራፊክ ደሴቶች ተውቦ የዘመናዊነት ማሳያ ሆኗል። ይህ የልማት መስመር እስከ ድሬዳዋ ምግብ ኮምፕሌክስ ዘልቆ የኮሪደሩ ዋነኛ አካል ሆኖ እናገኘዋለን።
የንግድ ታሪክ መናገሻ የነበረው ታይዋን የተመሰቃቀለው ገጽታው ቀርቶ በንጹሕ የእግረኛ ኮሪደርና በሥርዓት በተደራጁ ሱቆች ሲተካ፤ የከተማዋን ታሪክ የወሰነውና በጎርፍ አደጋው የሚታወቀው ደቻቱ ወንዝ በበኩሉ፤ የደራሽ ጎርፍና የውሃ መከማቸት ችግርን በሚፈቱ ዘመናዊ የውሃ ፍሳሽ ማስወገጃዎች፣ ቦዮችና ዳርቻው ላይ በተገነቡ ማራኪ መናፈሻዎች ታግዞ ከአስፈሪነት ወደ ማራኪ የቱሪስት መስህብነት ተቀይሯል።
ይህ ሁሉ ልማት ለድሬዳዋ ነዋሪዎች የሰጠው ትልቁ ስጦታ የክብር እና የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ነው። ፕሮጀክቱ በመላው የከተማዋ ክፍሎች ላይ ወጥ በሆነ መልኩ እየተተገበረ በመምጣቱ በርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎችን አምጥቷል።
ነዋሪው ማታ ማታ ወጥቶ በነጻነት የሚተነፍስባቸው፣ ህጻናት የሚጫወቱባቸው እና ወጣቶች የሚያነቡባቸው የአረንጓዴ መናፈሻዎችና የውሃ ፏፏቴዎች መፈጠራቸው የህዝብን የባለቤትነት ስሜት ከፍ አድርጎታል።
በሌላ በኩል ደግሞ በፕሮጀክቱ ትግበራ ሂደት ለበርካታ ወጣቶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ሰፊ የሥራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን፣ በኮሪደሩ ዳርቻ የተከፈቱ አዳዲስ ካፌዎችና ሱቆች ለአነስተኛና መካከለኛ ነጋዴዎች አዲስ የገቢ ምንጭ ሆነዋል።
ከዚህም ባለፈ በምሽት በሚደምቁ ዘመናዊ የመንገድ መብራቶች ምክንያት የከተማዋ የምሽት ኢኮኖሚ ከዚህ በፊቱ በበለጠ ነቅቷል፤ ከተማዋን ወደ ስማርት ሲቲ የሚያሸጋግሩ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መሙያ ጣቢያዎች እና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መካተታቸውም የነዋሪውን የደህንነት ስሜትና የቴክኖሎጂ ሽግግር አረጋግጠዋል።
ድሬዳዋ ዛሬም ያቺው የፍቅር እና የባቡር ከተማ ናት። ነገር ግን አሮጌውን የትናንት ካፖርቷን አውልቃ፣ ለኑሮ ምቹና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ዘመናዊ መልክ ተጎናጽፋለች።
የኮሪደር ልማቱ ድሬዳዋን በታሪኳና በነፍሷ ላይ አዲስ የወጣትነት መልክ የቀባ፣ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ውድ ስጦታ ያደረገ ድንቅ ስራ ነው። ይህ የልማት ጉዞ ኢንቨስተሮች በሆቴልና በሬስቶራንት ዘርፍ እንዲሁም የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግም በርካታ የጤና ተቋማት እየተገነቡ ወደስራ በመግባታቸው ከከተማዋ የእንግዳ ተቀባይነት ጋር ተዳምሮ አቅም እንዲያሳድጉ ትልቅ በር ከፍቷል።
ድሬዳዋ አሁንም የምስራቋ ንግሥት እና የሁሉም ኢትዮጵያዊ መኖሪያ በመሆኗ “ትንሿ ኢትዮጵያ” እስከመባል ደርሳ፣ አሁን ደግሞ በኮሪደር ልማት የተዋበ አዲስ የዘመናዊነት ዘውድ የደፋች ንግሥት ሆናለች።
በኃይለኢየሰሱ መኮንን

