አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለይም የከተሞች ነዋሪዎች የቤት ጉዳይን በችግርነት ያነሳሉ። ይህ ችግር የቤት አቅርቦት እጥረት እንዲኖር ከማድረግ እስከ ዜጎች የተጋነኑ የቤት ኪራይ ክፍያ መጠየቅ ይደርሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰኔ 30 ፣ 2018 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበራቸው ቆይታ አንድ ብስራት ለዚህ አንገብጋቢ የቤት ጥያቄ አብስረው ነበር።
“በቀጣይ አመታት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ይገነባሉ። ለዚህም የሚያስፈልገው የሞርጌጅ ስርአት ይገነባል።” ነበር ያሉት።
የቤት አቅርቦት እጥረቱን ከፈጠሩ ችግሮች መካከል የፋይናንስ አቅርቦት አለመኖር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ለዚህ ችግር እልባት የሚሰጥ ጅማሬ ወደ ተግባር መቀየሩን አብስረዋል።
ዛሬ ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) የደረሱበት ስምምነት፣ በሀገራችን የፋይናንስ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ የከፈተ ክስተት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)እንዳስታወቁት፣ ይህ ስምምነት ሀገራችን የመጀመሪያውን የተለየ የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ተቋም እንድትመሠርት የሚያስችል ታሪካዊ የትብብር ማዕቀፍ ነው።
ጉዳዩ ከቁጥሮች ባለፈ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የቤት ባለቤት የመሆን ህልማቸውን እውን ለማድረግ የተጣለ የፖሊሲ መሠረት ነው።
አዲሱ ተቋም በ100 ቢሊዮን ብር ካፒታል የሚቋቋም ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ደግሞ እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ አስተዋፅኦ ያደርግበታል።
ይህ ተቋም መልሶ ማጠናከሪያ በሚል ስልት የሚሠራ በመሆኑ፣ ባንኮች ለቤት ገዢዎች የሚሰጡትን የረዥም ጊዜ ብድር ሙሉ ለሙሉ ከራሳቸው ተቀማጭ ገንዘብ ከመሸፈን ይልቅ፣ ከዚህ ተቋም ተጨማሪ የገንዘብ ፍሰት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
ይህ መንገድ በዓለም ላይ በበርካታ ሀገራት የተሳካ ሞዴል ሲሆን፣ የቤት ብድር ገበያን ከባንኮች የአጭር ጊዜ ተቀማጭ ጫና ነፃ በማድረግ ዘላቂነት ያለው የቤት ፋይናንስ ሥርዓት ይፈጥራል።
እርምጃው ምን ችግር ይፈታል? የሚለውን እንጠይቅ…
እስካሁን በኢትዮጵያ የቤት ባለቤት መሆን ለብዙ ዜጎች የራቀ ህልም ሲሆን ኖሯል። ዋነኛው ምክንያትም ረዥም ጊዜ የቤት ብድር አቅርቦት ውስንነትና ከፍተኛ ወለድ ነው።
ይህ አዲስ ተቋም በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽ የሚሆን የቤት ብድር ፋይናንስ በማቅረብ፣ በተለይ በመካከለኛ ገቢ ላይ ለሚገኙ ዜጎች፣ ወጣቶች እና ለቤተሰብ መስራች ትውልድ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።
በተጨማሪም፣ 1.5 ሚሊዮን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገነቡ ቤቶች ግብ መያዙ፣ ከከተማ እስከ ገጠር ላለው የቤት እጥረት ችግር ተጨባጭ ምላሽ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህም ማለት ዜጎች ከኪራይ ውጣ ውረድ ተላቀው፣ የራሳቸውን ቤት ባለቤት በመሆን የኑሮ መረጋጋትና ማህበራዊ ክብር የማግኘት ዕድላቸው ይሰፋል ማለት ነው።
በአፈወርቅ እያዩ

