አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕብረተሰብን ጤና መጠበቅ ለዘላቂ ሀገራዊ ብልጽግና መሠረት ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው ወቅት እንዳሉት፤ የሕብረተሰብ ጤና ድምር ውጤቱ በተሰማራበት ዘርፍ ሁሉ ውጤታማ ተግባር የሚከውን እና ለሀገሩ ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚተጋ አምራች ሕብረተሰብ መገንባት ነው።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኢትዮጵያን ላለፉት 100 ዓመታት ያገለገለ፣ ታሪካዊ ወረት እና ዘመናዊ አቅምን ያጣመረ መሆኑን በመግለጽ የሕብረተሰብን ጤና መጠበቅ ለዘላቂ ሀገራዊ ብልጽግና መሠረት ነው ብለዋል።
ተቋሙ በወረርሽኝ ልየታ፣ በበሽታ ክትትልና ምላሽ፣ በላቦራቶሪ፣ በምርምር፣ በዲጂታላይዜሽን እና በጤና ስጋት ዝግጁነት የሀገሪቱን የጤና ሥርዓት በጥንካሬ እየደገፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በክልሎች የድንገተኛ ሕብረተሰብ ጤና አደጋ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከላትን ማቋቋሙና የሪፈራል ላቦራቶሪዎችን ማስፋፋቱ የሀገሪቱን የጤና ዝግጁነት አቅም እያጠናከረ ያለ ወሳኝ ተግባር መሆኑንም አንስተዋል።
በቀጣይም የአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና የልህቀት ማዕከል ለመሆን በከፍተኛ ትጋት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው የዓለም የጤና ድርጅት የትብብር ማዕከል በመሆን ዓለም አቀፍ ሚናውን ለማጠናከር ብርቱ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የትላንትን ታሪክ ጠብቆ፣ ዛሬን በዘመናዊነት ዋጅቶ፣ ወደ ነገ የሚገሰግስ እንደዚህ ያለ ተቋምን መደገፍና ማጠናከር ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢንስቲትዩቱ የሀገርን ብልፅግና ለማፋጠን ወሳኝ አቅም በመሆኑ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የሥራ እንቅስቃሴንም ጎብኝተዋል።
በተቋሙ የጀመረው የአኩቴክ ዲያግኖስቲክ ላቦራቶሪ በቀን ከ11 ሺህ 200 በላይ የሕሙማን ናሙናዎችን የመመርመር አቅም እንዳለው በጉብኝቱ ተነስቷል።
በተጨማሪም የሥነ ተዋልዶ ጤና የልህቀት ማዕከልን እና ለተሳካ የሕዝብ አገልግሎት አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኘውን የተቋሙን የጥሪ ማዕከል እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
በለይኩን ዓለም

