አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሪክስ መድረክ የጋራ ትብብርን ወደ የጋራ እሴት፣ ጽናት እና ዘላቂ ዕድገት የመለወጥ ሰፊ አቅምና ቁርጠኝነት አለው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ፥ ጽናትን፣ ፈጠራን፣ ትብብርን እና ዘላቂነትን መገንባት በሚል መሪ ቃል በሕንድ ኒው ዴልሂ እየተካሄደ በሚገኘው 18ኛው የብሪክስ ጉባኤ ላይ አካል በመሆናችን ኩራት ይሰማናል ብለዋል።
በብሪክስ አባል ሀገራት ዘንድ ሀብት፣ ቴክኖሎጂ እና ሰፊ ገበያ አለን፤ አሁን ያለውን መልካም ዕድል እነዚህን አቅሞች በማስተሳሰር የላቀ እሴት መፍጠር እና ይህ እሴት ደግሞ ሀብቱ በሚገኝበት ቦታ መመረት እንዲችል ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በማዕድን ልማት፣ በታዳሽ ኃይል እና እያደገ በሚገኘው የኢንዱስትሪ መሠረቷ ላይ እነዚህን አጋርነቶች ለመገንባት ዝግጁ ናት ሲሉም አመልክተዋል።
በተጨማሪም በአሠራር ሥርዓቶቻችን ውስጥ ጽናትን መገንባት፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የአህጉራችንን ፍላጎት እንዲያገለግል ማድረግ፣ አስተማማኝ የዕዳ እፎይታ ሒደትን ማሳደግ እንዲሁም የአየር ንብረት ጥበቃ ሥራዎችን ከኢኮኖሚ ሽግግር ጋር ማስተሳሰር ይኖርብናል ሲሉም አስገንዝበዋል።

