አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ቡና ለኢትዮጵያውያን የመሰባሰቢያ፣ ችግሮቻቸውን በውይይት የመፍቻ ቁልፍ ጊዜ ማግኛ እንዲሁም የታሪክ፣ የባህል፣ የማኅበራዊ ትስስር እና የኢኮኖሚ ዋነኛ መሠረት ነው።
በኢትዮጵያውያን ዘንድ ቡና ጠጡ ማለት እንዲሁ ዘልማዳዊ ብቻ አይደለም፤ ቡና ሲቀርብ የአብሮነት ቁርስ ይቀርባል፡፡
ሰዎች ተጠራርተው ቡና በሚጠጡባት ሰዓት ውስጥ ችግሮቻቸውን ይወያያሉ፤ የተጣሉትን ለማስታረቅ ቀጠሮ ይይዙበታል፤ በአጠቃላይ በርካታ ማኅበራዊ መስተጋብሮች ይከናወኑበታል።
በኢኮኖሚው በኩልም ቡና ለኢትዮጵያ አረንጓዴ ወርቋ ነው፤ የአረቢካ ቡና መገኛ እንደመሆኗ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው መጠን እንደመገኛነቷ የጎላ ነው።
የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ቡና፤ በዓለም አቀፍ ገበያ ባለው ተፈላጊነትና ጥራት ምክንያት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አቅም በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተከናወነው ሥራ ምርቱ ለጠቅላላው የግብርና ዘርፍ እመርታ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ክፍቷል።
የመጀመሪያውን የቡና ፍሬ ለቅማ እና ሰብስባ ለዓለም ያበረከተችው ኢትዮጵያ አሁንም ምርቱን አሳድጋ ዋናው የኢኮኖሚ ዋልታዋ ደጋፊ ለማድረግ ጠንክራ እየሰራች ነው።
በ2018 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከቡና ወጪ ንግድ 3 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ገቢ አግኝታለች፤ ይህ ገቢ ታዲያ ባለፉት 17 ዓመታት አጠቃላይ ካገኘችው 3 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ገቢ ጋር የሚቀራረብ ነው።
ኢትዮጵያ የቡና ሥርዓቷ በራሱ ትዕግስትን የሚያስተምር እና ስክነትን የሚያላብስ ነው።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርም የቡና ምርት ዕድገትን የሚያፋጥን የአየር ከባቢን ከመፍጠር ባለፈ የቡና ተክልን ለማስፋት የሚያስችል ሥራ የተሰራበት እና ወደፊትም የሚሰራበት ነው፤ ከሚተከሉ ችግኞች ሰፊውን ቁጥር የሚይዘው የቡና ችግኝ ነው።
የገበሬውን ጉልበት በብዙ የሚጠይቀው የቡና ምርት አንዳንድ ጊዜ የሚያጠቃው በሽታ ይከሰታል፤ ኢትዮጵያም ይህንን በሽታ ለመለየት እና ለማከም የሚያስችላትን የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ምርምሮችን እያሳደገች ትገኛለች።
በቀጣይ በቴክኖሎጂ በመታገዝ የቡና ምርትን ጥራት፣ ጤንነት እና ብሔራዊ ጠቀሜታ ለማጠናከር በቁርጠኝነትና በቅንጅት መሥራት ይገባል።
በእመቤት ሲሳይ

