አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 28 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የዲቾቶ – በለሆ የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ ፕሮጀክት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ መንገደኞች ባለስልጣን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መንግስት በአፋር ክልል የተገነባውና የ78 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ መንገድ አዲሱን የታጁራ ወደብ ለመጠቀም ያስችላል ተብሏል።
ከዚያም ባለፈ በነባሩ ጅቡቲ ወደብ ይፈጠር የነበረውን የትራንስፖርት ጫና እንደሚያቃልል ተገልጿል።
ከአስፋልት ይልቅ በሲሚንቶ ኮንክሪት ደረጃ የተገነባው ይህ መንገድ አካባቢው ባለው ከፍተኛ ሙቀት ተቋቋሞ ግልጋሎት የመስጠት አቅሙን የተሻለ እንደሚያደርገው ተገልጿል።
ከዚያም ባለፈ የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገድ በአነስተኛ ጥገና እስከ 40 አመት አገልግሎት መስጠት ስለሚያስችለው ለጥገና የሚወጣውን ወጪ በእጅጉ እንዲቀንስ ይረዳዋልም ነው የተባለው።
ፕሮጀክቱ የአገሪቷ የወጪ ገቢ ንግድ የሚካሄድበት ኮሪደር እንደመሆኑ መስመሩን የሚጠቀሙ በርካታ ቁጥር ያላቸው የጭነት ተሽከርካሪዎች ክብደት የመሸከምም አቅም እንዲኖራቸው ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተመላክቷል።
ከዚህ ባሻገር በአካባቢው ያለውን የፖታሽ ክምችትም ሆነ ሌሎች ማእድናት በቀላሉ በአቅራቢያ ወዳለ ወደብ ለማድረስ ያግዛል መባሉን ከኢትዮጵያ መንገደኞች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

