አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የጁቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦመር ጊሌ ከኢትዮጵያ ደወሌ የሚያገናኝና ታላቅ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት የሆነውን አዲስ የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታን ይፋ አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ ከፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦመር ጊሌ እና ከአሊኮ ዳንጎቴ ጋር በመሆን በጅቡቲ ዳመርጆግን ከኢትዮጵያ ደወሌ የሚያገናኝና ታላቅ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት የሆነውን አዲስ የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታን ዛሬ ይፋ አድርገናል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በሁለቱም ጫፎች ላይ በሚገነቡ የማከማቻ ተርሚናሎች የተደገፈ ሲሆን÷ ይህ ታሪካዊ መሰረተ ልማት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በዳንጎቴ ግሩፕ ጥምረት የሚተገበር ነው።
የሎጂስቲክስ ወጭንና መዘግየትን በመቀነስ፣ የኢነርጂ ዋስትናን ያጠናክራል፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ-ጅቡቲ የንግድ መስመርን ፍጥነት እና ዘላቂነትን ያሳድጋል ነው ያሉት።
መሰረተ ልማቱ ከነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታ በላይ፣ የአፍሪካውያንን ኢንቨስትመንት እና በጋራ መልማትን ማዕከል ያደረገ፣ ለዘላቂ እድገት፣ ለቀጣናዊ ትስስርና ይበልጥ አስተማማኝ ለሆነ የጋራ ኢኮኖሚያዊ እጣ ፈንታ የሚደረግ ሰፊ ኢንቨስትመንት ነው ሲሉም አውስተዋል።

