አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በኬንያ መንግሥት በዛሬው ዕለት የተጀመረው የላሙ የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክት ለቀጣናው የኃይል ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በኬንያ የላሙ የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክት ግንባታ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚጠቀሙት ነዳጅ አብዛኛውን ጊዜ ከአፍሪካ ውጭ ባሉ ሀገራት እንደሚመረት አስታውሰዋል፡፡
ይህም በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ጠቁመው÷ የላሙ የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በዓለም አቀፉ የነዳጅ ግብይት ዋጋ መጨመር ሳቢያ የሚደርስባቸውን ተፅዕኖ ይቀንሳል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ለአፍሪካ ገበያ ነዳጅ ማቅረብ እንደሚጀምር ጠቁመው÷ ይህም እያደገ ላለው የአህጉሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ገልፀዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኡጋንዳን በመሠረተ ልማት ለማስተሳሰር በታለመው የላፕሴት ፕሮጀክት አካባቢ እንደሚገኝ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህም ቀጣናዊ ንግዶችን ለማጠናከር እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ ቀጣናዊ አቅርቦት አማራጮቿን እንድታስፋፋ እንደሚያግዝ ጠቅሰው÷ ለቀጣናዊ ንግድ እና ኢንቨስትመንት አዲስ ዕድል እንደሚፈጥር አስገንዝበዋል፡፡
ይህ ቀጣናዊ ወሳኝ ፕሮጀክት እንዲጀመር አመራር የሰጡትን የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ እንዲሁም በአፍሪካ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን እያከናወኑ የሚገኙትን ናይጄሪያዊ ባለሃብት አሊኮ ዳንጎቴ አድንቀዋል፡፡
በዛሬው ዕለት የተጀመረው እና በዳንጎቴ ግሩፕ የሚገነባው የላሙ የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክት ከ16 ቢሊየን ዶላር በላይ የግንባታ ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን÷ በ2030 ተጠናቅቆ አገልግሎት እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡
በሚኪያስ አየለ

