አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ወደ ዕድል እየቀየረ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካው መስክ ታላላቅ ውጤቶችን እያስመዘገበ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢሬቻ በዓልን በማስመልከት ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት÷ ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ሆና ሳለች የስሟን ያህል ሳትጠቀም እና ልክ እንደ ስሟ ሳትሆን ረጅም ዘመናትን ማሳለፏን አውስተዋል።
ሀገሪቱ በርካታ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሃብቶች እያሏት በዕውቀትና በሥርዓት ስላልተመራች ብቻ እነዚህን ጸጋዎች ወደ ተጨባጭ አቅም መለወጥ ሳትችል መቆየቷንና በድህነት ተምሳሌትነት ስትጠቀስ መኖሯን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ረጅም ዘመናት ያስቆጠረ የሀገረ መንግሥትነት ታሪክ ቢኖራትም፤ የሕዝብን መሠረታዊ ችግር የሚፈታና ሀገርን የሚያሻግር ዘመናዊ አስተዳደር ለመገንባት ስትቸገር ቆይታለች ነው ያሉት፡፡
ከራሷ አልፎ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ማሳደር የሚያስችል ስትራቴጂካዊ የመልክዓ ምድር አቀማመጥ ቢኖራትም ሳትጠቀምበት መቆየቷን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷በዚህም ምክንያት በእህል ጎተራ ላይ ተቀምጦ የሚራብ፣ የውሃ ሀብት እያለው የሚጠማና እያለው ያጣ ሕዝብ ሆነን ኖረናል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ራዕይ ዕውን ለማድረግ የተያዘው ግብም በጠንካራ አንድነት ላይ የተመሠረተች፣ ሉዓላዊነቷ የተከበረ፣ በስፋት የምታመርት፣ ማንኛውንም ዓይነት ፈተና ተቋቁማ የምታልፍና ለአፍሪካ ግንባር ቀደም ተምሳሌት የሆነች ሀገርን መገንባት መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያን ወደ ታላቅ ስልጣኔ የማሻገር ስትራቴጂያዊ ዕቅድ በአሁኑ ወቅት በተግባር እየተተገበረ እንደሚገኝ ጠቁመው÷ የመደመር መንግሥት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ፈተናዎችን ወደ መልካም ዕድል በመቀየር በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች ታላላቅ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቁ፣ ሀገራዊ የምክክር ሒደት በተሳካ ሁኔታ መከናወኑ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካና የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክቶች መጀመራቸው እንዲሁም የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ መጀመር ለዚህ ታላቅ ስኬት አበይት ማሳያዎች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
እነዚህ ተግባራት የኢትዮጵያ የስልጣኔና የብልጽግና ጀንበር ብቅ እያለች ለመሆኗ ግልጽ ማረጋገጫዎች መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐበይ (ዶ/ር) በመልዕክታቸው አብራርተዋል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

