
ዛሬ ከተማና ገጠሩ እየተቀየረ ነው፤

ከተሞቻችን የዘመናዊ ከተማ መልክ ለመያዝ ጥረት ማድረግ ጀምረዋል፤

ዛሬ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ውብ አበባ ተብላ ብትጠራ እውነታ እንጂ ሙገሳ ተደርጎ አይወሰድም፤

መሶብ የኢትዮጵያን የአገልግሎት አሰጣጥ መልክ ሲያስተካክለው፤ ፋይዳ አዲሱን የዲጂታል ማንነት ሲያጠናክረው፤
የወንዝ ዳር ልማት የኢትዮጵያን የውኃ እሳቤ ሲቀይረው፤ የገበታ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን ነባር መልኮች በአዲስ መልክ ሲገልጡ በዓይናችን አይተናል፡፡

የአዲስ አበባ ለውጥ የዓለም ጉባኤዎችን ኑ ወደኔ እያለ ሲጣራ፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የምርት ባህላችንን ሲያድሰው፤ የማዕድን ልማታችን ለዘመናት የወጪ ንግዳችንን በአጭር ጊዜ መብለጥ ሲችል ለመታዘብ በቅተናል፡፡

እነዚህን ተስፋ ሰጪ ጅማሮዎች አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡

ባለፉት ዓመታት የመጣንበት መንገድ እንደ ኮሪደር የተስተካከለ፤ እንደ ወንዝ ዳር ልማት ያማረ አልነበረም ብዙ ፈተናዎችን አልፈናል፡፡

የኢትዮጵያ ለውጥ ያስደነገጣቸው አካላት በክፉ አይናቸው ያዩን ጀመር፡፡

የችግኝ ዋርካ ከሆነች አንችላትም ብለው ሰጉ፤ ስለዚህ ባልበላው ጭሬ አፈሰዋለው በሚለው ደካማ መንገድ ተነሱ፡፡

ከሮጠች አንይዛትም ብለው የመጨረሻውን ጥይታቸውን መተኮስ ጀመሩ፡፡

ባዳና ባንዳ ለእኩይ ዓላማ ተባበሩ፤ ሀገር ሻጭና ሀገር በታኝ ቀብድ ተቀባበሉ፡፡

በሰይፍም በሰልፍም፤ በውሸትም በሀሜትም፤ በተንኮልም በሽረባም ባገኙት የትግል ሜዳ ሁሉ ከጉዟችን ሊያደናቅፉን መከራቸውን አዩ፤ ኢትዮጵያን ግን አልቻሏትም፤ አይችሏትም፡፡