አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ከማዕድን ማውጣት እስከ ኢንዱስትሪ ሽግግር ድረስ በሀገራችን ውስጥ የላቀ እሴት እየፈጠርን እንገኛለን አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በሳም ፕሬሺየስ ሜታልስ መካከል በተደረገ አጋርነት በቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና የተገነባውን ብሔራዊ የውድ ማዕድናት ማጣሪያ ፋብሪካ በዛሬው ዕለት ስራ አስጀምረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ በዓመት ከ600 ቶን በላይ ውድ ማዕድናትን የማንጠር አቅም ያለው ይህ የማጣሪያ ፋብሪካ፤ በሀገር ውስጥ ምርት ላይ እሴት ለመጨመር፣ የኢትዮጵያን የማዕድን ዘርፍ ለማጠናከር እና ሀገራችንን በውድ ማዕድናት ማጣሪያ ረገድ ቀጣናዊ ማዕከል ለማድረግ ለተጀመረው ጉዞ ትልቅ ምዕራፍ ነው ብለዋል።
ይህ ውጥን፤ ሀብቶቻችንን ከኢንዱስትሪ አቅም ጋር በማስተሳሰር ወጭ ንግድ ገቢን ለማሳደግ፣ የሰለጠነ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የጌጣጌጥ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ፣ እንዲሁም ይበልጥ ግልጽ እና ተወዳዳሪ የሆነ የወርቅ እሴት ሰንሰለት ለመገንባት የመደመር መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡
ከማዕድን ማውጣት እስከ ኢንዱስትሪ ሽግግር ድረስ በሀገራችን ውስጥ የላቀ እሴት እየፈጠርን እንገኛለን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

