Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በማይነጥፈው የጀግንነት ተጋድሏችን የሰንደቅ ዓላማችን ክብር ከፍ እንዳለ ይቀጥላል – ሌተናል ጄኔራል አጫሉ ሸለመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በማይነጥፈው የጀግንነት ተጋድሏችን የሰንደቅ ዓላማችን ክብር ከፍ እንዳለ ይቀጥላል አሉ የመከላከያ የሰው ሀብት አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አጫሉ ሸለመ።
 
19ኛው ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን ከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖችና የሠራዊት አባላት በተገኙበት በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ተከብሯል።
 
ሌተናል ጄኔራል አጫሉ ሸለመ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ፥  ሰንደቅ ዓላማ በታላቅ መስዋዕትነት የተገኘ የኢትዮጵያውያን ዘመን የማይሸረው የማንነት መለያ ነው ብለዋል።

አክለውም ወታደሩ ሀገርና ሕዝብን ለመጠበቅ ቃል የሚገባው እንዲሁም የተሰጠውን ግዳጅ ፈጽሞ አሸናፊነቱን የሚያውጀው በሰንደቅ ዓላማው ፊት በመሆኑ ሰንደቅ ዓላም ለሠራዊቱ ልዩ ትርጉም እንዳለው አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያንና የቀጣናውን ሰላም ለማረጋገጥ የሠራዊቱን አቅም በወታደራዊ ቴክኖሎጂ የመገንባቱ ሥራ ከብሔራዊ ጥቅም አኳያ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

ሌተናል ጄኔራል አጫሉ ሸለመ ፥ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የሰንደቅ ዓላማ ክብር ለመዳፈር የሚሞክሩ ታሪካዊ ጠላቶችን ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ልክ እንደ ትላንቱ ሁሉ የሽንፈት ጽዋ እያጋታቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።

#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

Exit mobile version