አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊ እና በባለብዙ ወገን የጋራ ትኩረትን በሚሹ ጉዳዮች ላይ እጅግ ፍሬያማ የሆነ የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ውይይቱ በኢትዮጵያና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለውን እድሜ ጠገብ ወዳጅነት ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊና ተግባራዊ አጋርነት ለማሳደግ በሁለቱም ሀገራት በኩል ያለውን ቁርጠኝነት ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ በተመለከተ የሰጠችውን ማረጋገጫ ማድነቃቸውን ጠቁመዋል፡፡
የሁለትዮሽ ትብብራችንን ለማጠናከር እንዲሁም በቀጣናዊና ባለብዙ ወገን መድረኮች ቅድሚያ በምንሰጣቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ አብረን ለመሥራት ያለንን ቁርጠኝነት አረጋግጣለሁ ነው ያሉት።

