አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8 ፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የቄራ አልማዝዬ ስፖርት ሜዳ ታዋቂ ስፖርተኞችን አፍርቷል ፤ ዛሬም አዳዲስ የስፖርት ጀግኖች፣ የሀገር ኩራቶችና የድል ባለቤቶች እንዲፈልቁ እድሉን እየፈጠርን ነው አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
በዛሬው ዕለት የቄራ አልማዝዬ ስፖርት ሜዳ እና ሥልጠና ማዕከል በዘመናዊ መልኩ ተገንብቶ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በይፋ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡
ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ፥ ይህ ሜዳ በታሪኩ ለኢትዮጵያ ኩራት የሆኑ ታዋቂ ስፖርተኞችን አፍርቷል። ዛሬም ከዚህ ሜዳ አዳዲስ የስፖርት ጀግኖች፣ የሀገር ኩራቶችና የድል ባለቤቶች እንዲፈልቁ እድሉን እየፈጠርን ነው ብለዋል።
ሜዳው ከዚህ ቀደም በአቧራና በጢሻ ተሸፍኖ፣ ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ የማያመች ገጽታ እንደነበረው የገለጹት ከንቲባዋ፣ አሁን ግን ለወጣቶች እና ለታዳጊዎች አካታች የሆነ አገልግሎት እንዲሰጥ ሆኖ ስለተገነባ የችሎታቸው መድረክና የሕልማቸው ተስፋ ሆኖ ተመልሷል ነው ያሉት።
በከተማዋ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋታችን ለታዳጊዎችና ለወጣቶች ጤናማ ሕይወት እንዲሁም ለስኬት መንገድ እየከፈተ ነው ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ከንቲባ አዳነች አክለውም ከዚህ ሜዳ በሀገርና በዓለም መድረክ የሚያበሩ ታላላቅ ስፖርተኞች ይፈልቃሉ የሚል እምነት አለን ሲሉ የስፖርት ማዕከሉን ዘላቂ ፋይዳ አንስተዋል፡፡
ይህ የጋራ ሀብታችን ነው። እንጠብቀው፣ እንናልማበት፣ በጋራም እናሳድገው፤ ለወጣቶቻችን ዕድል እንፍጠር፤ ለሕልማቸው መንገድ እንክፈት፤ ለኢትዮጵያም አዲስ የድል ታሪክ እንጻፍ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

