አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕገ ወጡ ህወሓት ለሰብዓዊ ክብር እና ህይወት ቅንጣት ታክል ግድ የለውም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ላይ እንዳሉት፤ ሰይጣን ለማስመሰል እንደሚጥረው ሁሉ ሕገ ወጡ ህወሓት በአፉ ሰብአዊ ለመምሰል ይለፋል፤ ስለ ሰብአዊ ክብርም ይሰብካል፣ ይጮሀል።
በተግባር ግን ሕገ ወጡ ህወሓት ለሰብዓዊ ክብር እና ህይወት ቅንጣት ታክል ግድ የለውም ብለዋል፡፡
ሕገ ወጡ ህወሓት በትግሉ ወቅት በትግራይ ማህበረሰብ ላይ የከፋ ግፍ ማድረሱን አስታውሰዋል።
የትግራይ ወጣቶች ፈንጂ እየረገጡ እንዲያልቁ ይደረግ እንደነበር፣ ባለሀብት የሆኑ ተጋሩ አርሶ አደሮች መሳፍንት እየተባሉ በጉድጓድ ይታሰሩ እና ይገደሉ እንደነበር አብራርተዋል።
የትግራይ ነፃነት ግንባር ( ግሐት) አባላትን እና መሪዎችን እራት ጋብዘዋቸው በተኙበት ገድለዋቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ሁሉ በዚያን ጊዜ የነበረ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል።
ከድል በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጋዮች የማይጠቅሙ እየተባሉ ተዋርደው መባረራቸውን ጠቅሰው፤ ከባድመ ድል በኋላም በሀሳብ የተለዩትን ‘አንጃ’ እያሉ መጣላቸውን ገልጸዋል።
የፌደራል ስልጣንን ካጡ በኋላ ደግሞ በ2013 ዓ.ም ጦርነት የትግራይ ወጣቶች በጥይት እየተደበደቡ ህይወታቸውን አጥተዋል አካላቸውም ጎድሏል፤ በሰሞኑ ግጭትም ተመሳሳይ ተግባር ተፈፅሟል ብለዋል።
በእመቤት ሲሳይ

