አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ክላሽ ተሸክሞ የሚንከራተተው የትግራይ ወጣት እጅ የጠመንጃ ቃታ ከመሳብ ይልቅ በኮምፒውተር ላይ ማረፍ አለበት አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቆይታ÷ የትግራይ ወጣት ቦታው በዩኒቨርሲቲ፣ በንግድ፣ በእርሻ ሥራ እና በፋብሪካዎች ውስጥ መሆን እንደሚገባው አጽንኦት ሰጥተዋል።
በጦርነት ምክንያት ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው ወጣት ሕይወቱን ማጣቱን፣ አካሉ መጎዳቱንና የደረሰበት ሥነልቦናዊ ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ወጣቶች ታፍሰው ወደ ጦርነት እንዲገቡ መደረጉንና አሁንም ያልተመለሱ እንዳሉ አመላክተዋል።
ላላተመለሰው ወጣት የሕወሓት መሪዎች ከደርግ ጋር ለ50 ዓመታት ተዋግተዋል፤ አልሞቱም፣ አልቆሰሉም፤ ልጆቻቸውን ወደ ውጪ ሀገር ልከው፣ ቤተሰቦቻቸውን አዲስ አበባ አስቀምጠው በወርቅ ንግድና ሕንፃ ግንባታ ተንደላቅቀው እየኖሩ እናንተ ለምን ትሞታላችሁ፣ ትቆስላላችሁ? ሲሉ ጠይቀዋል።
የወጣቱ ሕይወት የራሱ እንጂ የድርጅት አለመሆኑን ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጣቱ ለእናትና አባቶቹ እንዲሁም ለትግራይ ሲል መኖር እንዳለበትና አካሉንና አእምሮውን ለልማት ማዋል እንደሚገባው መልዕክት አስተላልፈዋል።
አክለውም በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የልማት ሥራ እየተከናወነበ ባለበት ወቅት በትግራይ ክልልም ወጣቱ ክላሽ አውርዶ የመልሶ ግንባታና የልማት አካል መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
በዮናስ ጌትነት

