Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ቀጣናውን የሚመራው የኢትዮጵያ የኒውክሊየር ልማት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ አህጉር ፈጣን የህዝብ ቁጥር እድገት እና የኢኮኖሚ ሽግግር እያስተናገደች ትገኛለች።

በኢኮኖሚው  ሽግግር  ውስጥ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል ከሆኑት መካከል ደግሞ አስተማማኝና ዘላቂ የኢነርጂ አቅርቦት እንዲሁም የላቁ ቴክኖሎጂዎች ባለቤት መሆን አንዱ ነው።

በዚህ ዐውድ ውስጥ የምስራቅ አፍሪካ ማዕከል የሆነችው ኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይል ልማትን ብሔራዊ ስትራቴጂዋ በማድረግ ከቀጣናው ሀገራት እጅግ የረቀቀ እና ፈጣን ርምጃ በማሳየት ላይ ትገኛለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽንን በጎበኙበት ወቅት እንዳረጋገጡት፣ ይህ ዘርፍ ለሀገሪቱ የረጅም ጊዜ የልማት ርዕይ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አለው።

በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን መሪነት እንዴት በተግባር እያረጋገጠች ነው ለሚለው እስካሁን የከወነቻቸው ተግባሮች ምላሽ የሚሰጡ ናቸው።
 
ለአብነትም በርካታ የቀጣናው ሀገራት የኒውክሊየር ቴክኖሎጂን በፖሊሲ እና በንድፈ-ሀሳብ ደረጃ ብቻ ሲያጠኑ ዓመታትን አስቆጥረዋል። ኢትዮጵያ ግን ይህንን ልምድ በመስበር በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተጨባጭ ተግባር ተራምዳለች።

ከ30 በላይ ስትራቴጂካዊ ቦታዎች በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ተጠንተው፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት አዋጭነታቸው ተረጋግጧል።

አሁን ላይ ኮሚሽኑ ዲፓርትመንቶችን በግልጽ ለይቶ ወደ ፕሮጀክት ትግበራ የመሸጋገር ሙሉ ቴክኒካዊ ቁመና ላይ ይገኛል። ይህ ፈጣን የተግባር ሽግግር ኢትዮጵያን በምስራቅ አፍሪካ ግንባር ቀደም ያደርጋታል።
 
በሌላ በኩል ብዙ ሀገራት የኒውክሊየር ቴክኖሎጂን የሚያለሙት ለኃይል ምርት ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ራዕይ ግን ሁሉን አቀፍ ነው።

ይህ ቴክኖሎጂ እየገሰገሰ ያለውን የኃይል ፍላጎት ከመመለስ ባለፈ፤ በጤናው ዘርፍ የካንሰር ህክምናን ለማዘመን፣ በግብርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና በኢንዱስትሪ ሽግግር ውስጥ የላቀ ሚና እንዲጫወት ተደርጎ የተነደፈ ነው።

የማንኛውም አብዮት ዘላቂነት የሚወሰነው በትውልድ ቅብብሎሽ ላይ ነው። ዛሬ ላይ ከ30 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ያሏት ኢትዮጵያ፣ ለነገው የሳይንስ ሽግግር የማይጠጥፍ የዕውቀት ምንጭ አላት።

ዛሬ የምናስቀምጠው አስተማማኝ መሰረት፤ ተተኪው ትውልድ ነገ ዓለም በሚወዳደርባቸው እንደ ኒውክሊየር፣ ስፔስ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ባሉ መስኮች በልበ ሙሉነት እንዲሰለፍ ያደርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንዳሉትም “እኛ ትልቅ ሀገርና ትልቅ ህዝቦች ነን፤ ይህንን ለዓለም ማሳየት አለብን። ለልጆቻችን እኛ ጀምረንና አዘጋጅተን ከቆየናቸው እነሱ ጨምረው የኢትዮጵያን ብልጽግና ያረጋግጣሉ።”

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የኒውክሊየር ኃይል ልማት ሰላማዊ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና እጅግ ኃላፊነት የተሞላበት ነው።

ከተራ ምኞት ባለፈ በተጨባጭ ጥናቶች የታገዘው ይህ የቴክኖሎጂ ስራ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን መሪነት የሚያጸና እና የነገዋን ብልጽግና በተጨባጭ የሚያበስር ደማቅ የብርሃን ጎዳና ነው።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በሶስና አለማየሁ

Exit mobile version