አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦች ተፈጻሚ እንዲሆኑ አበክሮ ይሰራል አሉ አፈ ጉባኤ አህመድ ሽዴ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ያዘጋጀው የእውቅና እና ምስጋና መርሃ ግብር አካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ፍቃዱ ተሰማ፣ የምክር ቤቱ አባላት፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት አፈጉባኤ አህመ ሽዴ እንዳሉት ፥ ምክክሩ በኢትዮጵያ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በምክክርና በመግባባት እንደሚፈቱ ያሳየ ትልቅ ውጤት የተገኘበት ነው።
አራት ሺህ ኢትዮጵያውያን መክረው ለሀገር ግንባታ መሰረት አኑረዋል ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ለሰለጠነ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አብራርተዋል።
ምክር ቤቱ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን በአዋጅ ከማቋቋም ጀምሮ ለስራዎቹ ስኬትማነት ሃላፊነቱን ሲወጣ መቆየቱንም አንስተዋል።
በቀጣይም በምክክሩ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ እንዲሁም ወደ ህግ የሚቀየሩ ጉዳዮችም ተቀይረው ስራ ላይ እንዲውሉ ምክር ቤቱ አበክሮ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ማገልገል ለኛ ክብር ነው፤ ዛሬ የተሰጠን እወቅናም በክብር የምንቀበለው ነው ብለዋል።
ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ ኮሚሽኑ አካታች ሂደትን መከተሉን አመልክተው፤ የምክክሩ ሂደት በዓለም አቀፍ ደረጃም ጭምር አውቅና የተቸረው ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በምክክሩ የተለዩ ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ የባለድርሻ አካላት ሚና ሊጠናከር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

