አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር መከላከያ ሠራዊት በተፈተነባቸው ሜዳዎች ሁሉ በጽናት አልፎ ድልን የተቀዳጀ ሀገርን ለሁለንተናዊ ከፍታ የሚያበቃ የድል ሰራዊት ነው አሉ የመከላከያ ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ።
119ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን “የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው ዕለት እየተከበረ ነው።
አቶ መሐመድ እድሪስ በበዓሉ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በጽናት ለመጠበቅ፣ ዘላቂ ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን እንዲሁም የህዝቡን ሁለንተናዊ ደህንነት ለማረጋገጥ በግዳጅ ላይ ለሚገኙ የሠራዊት አባላት ምስጋና አቅርበዋል።
ለሀገርና ለወገን ዘብ ከመቆም የበለጠ ታላቅ ክብር የለምና የምትከፍሉትን እስከ ህይወት የሚደርስ ውድ መስዋዕትነት በከፍተኛ ሀገራዊ አክብሮት በመገንዘብ በዚህ ታሪካዊ ቀን ላቅ ያለ ልባዊ ምስጋና ላቀርብላችሁ እወዳለሁ ብለዋል።
በጽናትና በጀግንነት የታነጸው ሠራዊታችን የሀገራችንን ህልውና የተፈታተኑ በርካታ ፈተናዎችን ድል አድርጓል በማለት ገልጸዋል።
ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ነጻነትና ታሪካዊ ኩራት በተግባር ያስመሰከረ እውነተኛ የድል ባለቤት መሆኑን ተናግረዋል።
የድል ሠራዊት ማለት በጦር ግንባር ጠላትን መክቶ ከመመለስ ባሻገር ሀገሩንና ህዝቡን ለሁለንተናዊ ድል፣ ለዘላቂ ሰላምና ለብሩህ ዕድገት የሚያበቃ ጠንካራ ተቋማዊ አቅምና ራዕይ ያለው ሠራዊት ማለት እንደሆነም አብራርተዋል።
መከላከያ ሠራዊቱ በተፈተነባቸው ሜዳዎች ሁሉ በጽናት አልፎ ድልን የተቀዳጀ ሀገርን ለሁለንተናዊ ከፍታ የሚያበቃ የድል ሠራዊት መሆኑን አብራርተዋል።
ለአፍታም ቢሆን ሳይናወጥ የሀገራችንና የህዝባችንን ሰላም ዋነኛ ተልዕኮ አድርጎ ተልዕኮው አድርጎ የተነሳው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን በከፈለው ተጋድሎ ታሪክ ሲዘክራቸው የሚኖሩ አበይት ድሎችን አስመዝግቧል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎችንና ማዕበሎችን ተሻግራ በተደላደለ እና አስተማማኝ መሰረት ላይ ሆና ወደ ታላቅነቷ የምትገሰግስበት አዲስ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
በመልካም ፈቃዱ

