አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀጨኔ–አምባሳደር–ጊዮን-ኢሬቻ–ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማትን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ይህ የ351 ሄክታር አጠቃላይ ስፋት እና የ10 ኪ.ሜ ርዝማኔ ያለው የኮሪደር ልማት ዘመናዊ፣ አረንጓዴ እና ሁሉንም አካታች የሆነች አዲስ አበባን የመገንባት ራዕያችንን እውን የሚያደርግ ትልቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
በዘመናዊ መሠረተ ልማት የታጀበው ይህ ልማት በቂ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች እና ከ100 በላይ መኪኖችን በአንድ ጊዜ መሙላት የሚያስችሉ ስምንት የኤሌክትሪክ መኪና መሙያ ማዕከላት አሉት ሲሉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም በወንዝ አስተዳደር፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም በወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ስፍራዎች አማካኝነት የአካባቢ ጥበቃን ከከተማ ገፅታ ለውጥ ጋር ማቀናጀት ተችሏል ብለዋል፡፡
ልማቱ አካባቢያዊ ገፅታውን ከማሳደግ ባለፈ አዳዲስ የኢኮኖሚ ዕድሎችን የፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።
የተዘጋጀው የገበያ ማዕከል ቀደም ሲል በወንዝ ዳርቻው ይኖሩ ለነበሩ ነዋሪዎች የዕደ ጥበብ ምርቶችን እንዲያመርቱ፣ ለማሳያና ለመሸጫ እንዲጠቀሙበት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የግብርና ምርት መሸጫ ማዕከል ደግሞ የግብርና አምራቾችን ከገበያው ጋር ያገናኛል ነው ያሉት።
ፕሮጀክቱ በውስጡ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን፤ እንዲሁም የተቀናጁ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን የያዘ በመሆኑ ለኑሮ ተስማሚና ተደራሽ የሆነ የከተማ ከባቢን እንደሚፈጥር አመልክተዋል፡፡
በተጨማሪም የልጆች መጫወቻ ስፍራዎች፣ ፕላዛዎችና አምፊ ቲያትሮች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች እንዲሁም የውሀ ትሪዒት ማሳያዎች ለመዝናኛና ማህበራዊ ግንኙነት አዲሰ ዕድል እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል፡፡
የእኛ ርዕይ ለዛሬውና ለሚቀጥሉት ትውልዶች ውብ ብቻ ሳትሆን ምርታማና ሁሉንም አካታች እንዲሁም ህዝቧን የምትመጥን ከተማ መገንባት ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።

