አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር ህልውና ምሰሶ ነው አሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ።
119ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን “የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው ዕለት እየተከበረ ነው።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጥንታዊ ከሚባሉ ሀገረ መንግሥታት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ጠንካራ ተቋማት ከገነቡ ሀገራት ተርታ ትመደባለች ብለዋል።
119 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ኢትዮጵያ ከገነባቻቸው አንጋፋ ተቋማት ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰው፤ ተቋሙ ከውጭ ጠላት እና ከውስጥ ባንዳዎች ጋር እየተዋጋ ሀገር ማጽናቱን ገልጸዋል።
የሀገርን ሉዓላዊነት እና አንድነት መጠበቅ የመከላከያ ሠራዊት ተልዕኮ መሆኑን በመጥቀስ፤ መከላከያ ሠራዊት የሀገረ መንግሥት ስርዓት እና የሀገር መኖር አለመኖርን የሚወስን የህልውና ምሰሶ ነው ብለዋል።
ሠራዊት የፖለቲካ አንጃ እና ሸማቂ አካላት ተባባሪ መሆን እንደማይችል ገልጸው፤ ይህን አደረገ ማለት ከተፈጥሮ ባህሪው በመውጣት ሀገር እንድትፈርስ ፈቀደ ማለት ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በአሁኑ የዲጂታል ዘመን መከላከያ ሠራዊትን እናፈርሳለን የሽግግር መንግሥት እናመጣለን የሚሉ ደፋር ባንዳዎች ተፈልፍለዋል ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ ሀገር ለማፍረስ የከጀሉ ደፋር ባንዳዎች በታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች የሚነዱ ናቸው ብለዋል።
በዚህ ዓመት መስከረም 13 ከግብፅ፣ ሱዳን እና ኤርትራ የተቀናጀ ፅምዶ መላላክ የተጠናወተው ህገ ወጡ ህወሓት እራሱ በከፈተው ጦርነት እንዳልነበር ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል።
በእመቤት ሲሳይ

