አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ደርሷል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ ኢትዮጵያ በመከላከያ ኃይሏ እያደረገችው ያለው ዝግጁነት ማንኛውንም ጥቃት ቀድሞ ማስቀረት የሚያስችላትን አስተማማኝ አቅም እያላበሳት ይገኛል።
ከሩሲያ መንግሥት ጋር በተደረገው ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹን አስራ ሁለት የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄቶች (Su-35 4++ Generation) ተረክባለች ብለዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ አራት የኤስ-400 (S-400) ዘመናዊ የአየር መከላከያ ስርዓት ባትሪዎችን እንደምትረከብ ገልጸዋል።
እነዚህን ዘመናዊ የጦር ጄቶች በመታጠቅ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ መሆን የቻለች ሲሆን፤ ይህም የሀገሪቷን ሉዓላዊነት ይበልጥ የሚያጠናክርና ወደፊትም የጋራ ደህንነትንና ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጉዞ በልበ ሙሉነት ለመቀጠል ትልቅ አቅም እንደሚሆን አመልክተዋል።
ይህንን ታሪካዊ ስኬት አስመልከቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከስምምነታችን አንድ ዓመት አስቀድሞ እነዚህን የጦር አውሮፕላኖች እንድንረከብ ስላሳዩት ትጋት ላመሰግናቸው እወዳለሁ” ብለዋል።

