Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ ሰማይ፣ በኢትዮጵያ እጅ!

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኤሮስፔስ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያሳየችው ፈጣን ሽግግር፣ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ከመሆን አልፎ የራሷን የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) በሀገር ውስጥ በስፋት ወደ ማምረት የተሸጋገረበትን አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።

ይህ ስትራቴጂካዊ ርምጃ የሀገሪቱን ታሪካዊ የማይበገር የነፃነት እና የፅናት መንፈስ ከዘመኑ የዲጂታል እና የኤሮኖቲክስ ምጥቀት ጋር ያጣመረ ትልቅ የሉዓላዊነት ማረጋገጫ ሆኗል።

የኢትዮጵያ የድሮን ማምረት እንቅስቃሴ የመደመር መንግሥት ቃላትን ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ መሠረተ ልማት እና በሀገር በቀል እውቀት የተደገፈ ተግባር እንደሚከውን ማሳያ ነው።

የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ስራ የጀመረው ስካይዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ የዚሁ ትልቅ ጥረት አካል ሲሆን ለደኅንነት፣ ለመረጃ ስምሪት፣ ለሲቪልና ለወታደራዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ድሮኖች ምርት በከፍተኛ ጥራት በማምረት ላይ ይገኛል።

በተጨማሪም በአዲስ አበባ የሚገኘው ኤሮ ዓባይ የተሰኘው ሁለተኛው ዋና የማምረቻና የመገጣጠሚያ ማዕከል የሀገር ውስጥ የኤሮኖቲክስ ኢንጂነሪንግ አቅምን በማጎልበት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል።

ይህ ተጨባጭ ውጤት የመጣው በኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (INSA) እና በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የተቀናጀ የምርምር እና ልማት ማዕቀፍ አማካኝነት የድሮኖቹ የሶፍትዌር፣ የሃርድዌር እና የሴንሰር ቴክኖሎጂዎች በሀገር ውስጥ አቅም እንዲበለጽጉ በመደረጉ ነው።

የኢትዮጵያ ተራራማና ከፍተኛ መልክአ-ምድር ለወትሮው የኤሮስፔስ ምርቶች ፈታኝ ቢሆንም፣ በሀገር ውስጥ የተሰሩት ድሮኖች ግን ይህንን ተፈጥሯዊ ገጽታ እንደ እድል ተጠቅመውበታል።

ምርቶቹ በተራራማ መልክአ-ምድር ውስጥ ያለ እንከን በከፍተኛ ቅልጥፍና የመብረር አቅም እንዲኖራቸው ተደርገው የተነደፉ ናቸው።

ከዚህም ባለፈ ምስሎችን በቅጽበት የመተንተን፣ ኢላማዎችን የመለየት እና ያለ ሰው ንክኪ የመብረር አቅም ያላቸው ዘመናዊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሶፍትዌር ስርዓቶች ተገጥመውላቸዋል።

ይህ የቴክኖሎጂ አብዮት የሀገሪቱን የደህንነት እና የልማት ፍላጎቶች በአንድ ላይ ያቀናጀ ሁለገብ ተግባር አለው።

በደህንነቱ ዘርፍ ድንበሮችን ከወራሪዎች እና ከስጋቶች መጠበቅ የሚያስችሉ የክትትል፣ የኤሌክትሮኒክስ ውጊያ እና በትክክለኛ ኢላማ ላይ ያተኮሩ የማጥቃት አቅም ያላቸው ድሮኖች ተሰልፈዋል።

በሌላ በኩል በሲቪል አገልግሎት ዘርፍ ሰፊ የግብርና መሬቶችን ከአየር ላይ የመከታተል፣ ፀረ-ተባይ መድኃኒቶችን የመርጨት እንዲሁም ለከተማ ፕላን እና ለመሠረተ ልማት ዝርጋታ የሚያገለግሉ የጂኦስፓሻል ካርታዎችን በጥራት የማዘጋጀት ተግባር ያከናውናሉ።

በሀገር ውስጥ ድሮኖችን ማምረት የቴክኖሎጂ ሽግግር ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ሉዓላዊነት የሚያጠናክር ስትራቴጂካዊ ርምጃ ነው።

በውጭ ሀገራት የቴክኖሎጂ ጥገኝነት ላይ የነበረውን ስጋት በማስቀረት ሀገራዊ ደህንነትን በራስ አቅም ማረጋገጥ ተችሏል።

በተጨማሪም ለኤሮስፔስ ምርቶች ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ብቻ ሳይሆን፣ ምርቶቹን ለምስራቅ አፍሪካ እና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለማቅረብ ሰፊ እቅድ ተነድፏል።

ይህ ሂደት ለወጣት መሐንዲሶች፣ የሶፍትዌር አልሚዎች እና ተመራማሪዎች ሰፊ የቴክኖሎጂ ማደጊያ እድል የፈጠረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ታሪካዊ የፅናት እሴቷን ከዘመናዊ የሳይንስ ምጥቀት ጋር በማዋሃድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የማይበገር አቅም እየገነባች መሆኗን ያረጋገጠ ነው።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በሶስና አለማየሁ

Exit mobile version