አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የፋይናንስ አገልግሎቶችን የበለጠ ተደራሽ፣ ምቹ እና ቀልጣፋ በማድረግ የባንክ ኢንዱስትሪውን ጉዞ እየለወጠው ይገኛል አሉ የአዋሽ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፀሀይ ሽፈራው ።
አዋሽ ባንክ በሃገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ የሚገኘውን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር በማስመልከት፣ በሳይበር ደህንነት ተግዳሮቶችና መፍትሄዎች ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት እያካሄደ ይገኛል።
“የሳይበር ደህንነት የሁሉም ኃላፊነት ነው” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው መርሐ ግብር የባንኩን የዲጂታል ደህንነት ማዕቀፍ ለማጠናከር፣ የሰራተኞችን የጥንቃቄ ግንዛቤ ለማሳደግ እና የሳይበር ጥቃቶችን አስቀድሞ ለመከላከል ያለመ ነው።
የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፀሐይ ሽፈራው በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፥ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የባንክ ኢንዱስትሪውን ጉዞ እያቀላጠፈው ይገኛል።
ከዚህ የዲጂታል ጉዞ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ውስብስብ የሳይበር ስጋቶችን ለመከላከል ግንዛቤን ማሳደግና ተቋማዊ የመቋቋም አቅምን ማጠናከር ቀዳሚ ዓላማ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ-ግብሩ የሳይበር ደህንነት ግንዛቤን ለማሳደግና እየተባባሰ የመጣውን የሳይበር ስጋቶችን ተቋማዊ የመቋቋም አቅም ለማጠናከር ዓላማ ያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የሳይበር ደህንነት የእያንዳንዱ ሰራተኛ፣ የደንበኛ የንግድ አጋር እና የባለድርሻ አካላት የጋራ ኃላፊነት መሆኑንም ዋና ስራ አስፈጻሚዉ ተናግረዋል።
የደንበኞችን እምነት መጠበቅ፣ ምስጢራዊ መረጃዎችን መጠበቅ እና የፋይናንስ ግብይቶችን ደህንነት እና ታማኝነት ማረጋገጥ ባንኩ ከሚሰጣቸው ዋና ዋና አገልግሎቶች ዉስጥ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በመሆኑም ባንኩ ዲጂታል ሀብቶቹን በመጠበቅ፣ የደንበኞችን መረጃ በመከላከል እንዲሁም አስተማማኝ፣ ታማኝ እና ጠንካራ የዲጂታል ባንክ አገልግሎቶችን በማረጋገጥ ረገድ ቁርጠኝነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በሲፈን መኮንን

