አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት በማጠናከር የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል አሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ።
የጤና ሚኒስቴርና የክልል ጤና ቢሮ ኃላፊዎች የጤና ሴክተር የጋራ ግምገማ መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።
ዶ/ር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት ፥ የጤና አገልግሎትን በፍትሐዊነት ተደራሽ በማድረግ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ ብለዋል።
የ2019 በጀት ዓመት ከሕዝብ ትልቅ አደራ የተቀበልንበትና የኅብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በከፍተኛ ትጋትና ቁርጠኝነት የምንሠራበት ወቅት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ አሠራር ነክ ማነቆዎችን በመቅረፍ ሕዝቡ ተገቢውን አገልግሎት በፍትሐዊነት እንዲያገኝ ማድረግ የትኩረት ማዕከል መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሚኒስትሯ የተሻለ ትውልድ ተሻጋሪ የጤና ስርዓት ለመገንባት የአመራሩ ቅንጅታዊ ትግበራ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
በመድረኩ የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና የመደመር መንግሥት የጤና ስትራቴጂ ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል።

