Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያን የእስልምና ታሪክና መንፈሳዊ እሴቶች ለሀገረ መንግሥትና ለሥልጣኔ ግንባታ ማዋል ያስፈልጋል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተስመገን ጥሩነህ

የኢትዮጵያን የእስልምና ታሪክና መንፈሳዊ እሴቶች ለሀገረ መንግሥትና ለሥልጣኔ ግንባታ ማዋል ያስፈልጋል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተስመገን ጥሩነህ።

የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት 2ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ተካሂዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን የእስልምና ታሪክና መንፈሳዊ እሴቶች ለሀገረ መንግሥትና ለሥልጣኔ ግንባታ ማዋል ያስፈልጋል።

የነቢዩ ዩሱፍ ታሪክ በቅዱስ ቁርዐን ከሚገኙ ታላላቅ ትምህርቶች አንዱ እንደሆነ በማንሳት የቤተሰብ ፍቅርንና ክህደትን፣ መከራንና ፈተናን፣ በመጨረሻም በእምነትና በፅናት እውነትን ማሸነፍን ያስተምረናል ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያም በታሪኳ ብዙ ሤራዎችንና መከዳቶችን አልፋለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተተበተቡባትን ወጥመዶች ሁሉ በጣጥሳ ወደ ተገባት ክብርና ሥልጣኔ እንደምትመለስ ያለን እምነት ጽኑ እንደሆነ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በእስልምና ታሪክ ልዩ ቦታ ያላት ሀገር ናት፤ የነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) አሳዳጊ የኡም አይመን፣ የመጀመሪያው ሙአዚን ቢላል፣ የመጀመሪያው ሂጅራ እና የነጃሺ ምድር ናት፤ አራተኛዋ የሙስሊሞች ቅዱስ ከተማ ተብላ የምትጠራው ሐረር መገኛም ናት ብለዋል።

ይህንን ታሪካዊና ባህላዊ ቅርስ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ፣ ለቱሪዝምና ለዓለም አቀፍ ግንኙነታችን በሚገባ ልንጠቀምበት እንደሚገባም አመልክተዋል።

የመደመር መንግሥት መንፈሳዊነትን እንደ ታላቅ ሀገራዊ ኃይል እንደሚመለከተው እና ይህንን ኃይል በአግባቡ ከተጠቀምንበት ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት እንደሚቻል ገልጸው መንግሥትም የሃይማኖት ተቋማት ጠንካራና ብቁ እንዲሆኑ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

እኛ ለሀገራችን ያልሠራነውን ማንም አይሠራልንም፤ እኛ ያላሳደግናትን ማንም አያሳድግልንም፤ እኛ ሰላሟን ያልጠበቅንላትን ሀገር ማንም አይጠብቅልንም ነው ያሉት።

“ለሕዝብ እጅግ የሚጠቅሙ ሰዎች፣ እነርሱ በአላህ ዘንድ እጅግ የተወደዱ ናቸው” እንደተባለው የሕዝባችንን ኑሮ፣ ጤና፣ ትምህርትና ሰላም የሚያሻሽል፤ የኢትዮጵያን የመደመር ሥልጣኔ የሚገነባ በጎ ሥራ ሠርተን ልናልፍ አደራ እላለሁ ብለዋል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

Exit mobile version